ቀጥታ፡

የቼክ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበላቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017(ኢዜአ)፦ የቼክ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በኢትዮጵያ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቢዝነስ ፎረም በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ዕድሎችን የማስተዋወቅ አላማ ባደረገው በዚህ ፎረም ላይ በርካታ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በቢዝነስ ፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል ጠንካራ ንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መመስረት የሚያስቸሉ መልካም ዕድሎች እንዳሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የተገበረችው ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻ እንዳደረጋት አመልክተዋል።

ስለሆነም የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎችም በተፈጠረው መልካም ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኮምቤ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ሕግጋት ማበረታቻዎችና ዕድሎች ዙሪያ ገለጻና ለቀረቡ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ስምንተኛው የኢትዮጵያ እና የቼክ ሪፐብሊክ የፖለቲካ ምክክር ትኩረት ከሰጣቸው ዋንኛ ጉዳዮች መካከል የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ማጠናከር አንዱ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የፖለቲካ ምክክሩ ዛሬ በፕራግ መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም