ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት አበክራ እየሰራች ነው -ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ጥር 26/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የመድኃኒት ግብዓቶችን በራስ አቅም ማምረትን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

156ኛው የዓለም ጤና ድርጅት (ደብሊውኤችኦ) የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብስባ በድርጅቱ ዋና መቀመጫ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ዛሬ ተጀምሯል።

በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በስብባው ላይ ተሳታፊ ሆኗል።

ዶክተር መቅደስ በስብስባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ብለዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አገልግሎት፣በአገር ውስጥ አቅም የመድኃኒት ግብዓቶችን ማምረት፣የጤና ፋይናንስ እና የሰለጠነ የጤና ባለሙያ ማፍራት እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

ሚኒስትሯ፥ የጤና ስርዓትን ለማጠናከር እና የማይበገር አቅምን ለመገንባት በሚደረጉ ጥረቶች ትብብር እና አጋርነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ዶክተር መቅደስ በንግግራቸው ከነሷቸው አንኳር ነጥቦች መካከል የዓለም የጤና ድርጅት በጤናው ዘርፍ ዓለም አቀፍ አቀፍ ደረጃን በማውጣት እየተወጣ ያለውን ልዩ ሚና ነው።

ከዚህም አንጻር ሀገራት የድርጅቱን መመዘኛዎች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም እና በመተግበር ለውጥ ለማምጣት እያከናወኑት ያለውን ስራ መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ ፥ በቅርቡ ዓለም አቀፍ የጤና ደንቦችን በማሻሻል ለተገኙ ስኬቶች እውቅና እንደምትሰጥ ገልጸው፥ ሁሉም አባል ሀገራት እ.አ.አ ሜይ 2025 የድርጅቱ የወረርሽኝ መከላከል ድርድሮች እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

156ኛው ደብሊውኤችኦ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ የፕሮግራም በጀት እና ዘላቂ ፋይናንስ ጨምሮ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብስባ እስከ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም