ቀጥታ፡

የተረጂነት አስተሳሰብን ለማስወገድ የሚዲያው ሚና ከፍተኛ ነው - አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017 (ኢዜአ) ፦የተረጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ ረገድ የሚዲያው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

የመንግስት ከሙኒኬሽን አገልግሎት፣የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከሚዲያዎች ጋር በጋራ ያዘጋጁትን ዘጋቢ ፊልምች በአፍሪካ ልህቀት ዓመራር አካዳሚ ተገምግሟል።

ፊልሞቹ ኢትዮጵያውያን ከተረጂነት እና ልመና በማላቀቅ ወደ ምርታማነትና ለጋሽነት ለማሸጋገር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠርን አላማ ያደረጉ መሆናቸው ተመላክቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በማህበረሰብ ውስጥ የሚታየውን የተረጂነት አስተሳሰብ ለመቀየር የሚዲያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ክብር የሚረጋገጠው በምግብ ራሳችንን ስንችል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ተረጂነት እና ልመና ኢትጵያውያንን አይመጥንም ብለዋል።

በደም ያስከበርነውን ነጻነታችንን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም በላባችን በማጽናት ሉዓላዊነታችንን ማስከበር ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በበኩላቸው ልመና እና ተረጂነት በእጅ አዙር በቅኝ መገዛት እና ዘመናዊ ባርነት ነው ብለዋል።

ልመና እና ተረጂነትን የሚጸየፍ ትውልድን ከመቅረጽ እና ማህበረሰቡን ከማንቃት አንጻር ከሚዲያው ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅ መግለጻቸውን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም