ቀጥታ፡

ለውሃ አዘል መሬቶች ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግ እየተሰራ ነው-የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017(ኢዜአ)፦ለውሃ አዘል መሬቶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ በአካባቢና በብዝሃ ህይወት ላይ ሊከሰት የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት መጠበቅና መጠቀም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።

የመግባቢያ ስምምነቱን የአካበቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከግብርና፣ውሃና ኢነርጂ፣መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴሮች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ነው የተፈራረመው።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ፥ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ ውሃ አዘል ወይም ረግረጋማ መሬት በመኖሩ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ያለውን ሚና ለማሳደግ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ አካባቢን እና የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

የውሃ አዘል መሬቶችን መጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተው፣ የተጀመሩ ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

የውሃ አዘል መሬቶች ለግብርና እና ቱሪዝም ልማት፣ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ጨምሮ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።

ውሃ አዘል ወይም ረግረጋማ መሬቶችን በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ካልተቻለ የመድረቅና የመጥፋት አደጋ ያጋጥማቸዋል ነው ያሉት።

ይህም በብዝሃ ህይወት መጥፋት ላይ አደጋ ከመፍጠር ባለፈ አካባቢ ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማስተዳደር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለውሃ አዘል መሬቶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ በአካባቢና በብዝሃ ህይወት ላይ ሊከሰት የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስራዎቹን በተቀናጀ መልኩ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተቀናጀና ውጤታማ የውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም መፍጠር እንደሚያስችል ነው የገለጹት።

የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈረሙት መካከል የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ እንዳሉት ኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ መንገዶች ያገኘቻቸውን የውሃ አዘል መሬቶች ባልተገባ መንገድ ጥቅም ላይ መዋለ እንደሌለባቸው ተናግረዋል።

እነዚህን ሃብቶች በዘላቂነት ተጠብቀው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲያስገኙ የቅንጅት ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በባለስልጣኑ የውሃ አካላትና ውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀምና ቁጥጥር ዴስክ ሃላፊ ዘሪሁን መንገሻ የመግባቢያ ሰነዱ ላይ ተቋማት ውሃ አዘል መሬቶችን ከጉዳት ለመታደግ ቅንጅታዊ አሰራሩን የበለጠ ማጠናከር የሚችሉበት አሰራር መያዙን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ 2 በመቶ ያህሉ መሬት ውሃ አዘል መሆኑን ቀደም ባሉ ዓመታት የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም