ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ለተፈራረሟቸው ስምምነቶች ተፈጻሚነት በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ለተፈራረሟቸው ስምምነቶች ተፈጻሚነት በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በተለያዩ መስኮች የተፈራረሟቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተፈጻሚነት በልዩ ትኩረት ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ስምንተኛው የኢትዮጵያ እና የቼክ ሪፐብሊክ የፖለቲካ ምክክር ዛሬ በኘራግ ተካሄዷል።
በምክክሩ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ ልዑካን ቡድን ተሳትፏል።
በቼክ ሪፐብሊክ በኩል የሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂሪ ኮዛክ፣የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣የቼክ ልማት ትብብር ኤጀንሲ እንዲሁም የቼክ ንግድና ኤኮኖሚ ዲፓርትመንት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በምክክሩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ያላቸውን ጠንካራ እና ታሪካዊ የዲኘሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀና ሁሉን አቀፍ ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል የተካሄዱ የከፍተኛ መንግስት ባለሥልጣናት የጉብኝት ልውውጦች መጨመር በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በመደበኛነት የሚካሄደው የፖለቲካ ምክክርም ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት፣በቱሪዝም፣በትምህርት፣በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የትብብር ማዕቀፍ መሠረቱን ለማስፋትና የበለጠ እንዲጠናከርም ያግዛል ነው ያሉት።
በምክክሩ ላይ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደሩ የቼክ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውም የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኘሮግራሞች የፈጠሯቸውን አመቺ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂሪ ኮዛክ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክን የጋራ ተጠቃሚነት ያማከሉ በርካታ የትብብር ዕድሎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጁ ናት ብለዋል።
የፖለቲካ ምክክር መድረኩ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና የተፈረሙ ስምምነቶችም ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል ቁልፍ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች ስምምነቶቹ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተውና ተቀራርቦ ለመስራት ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከፖለቲካ ምክክር በተጨማሪ ከቼክ ሪፐብሊክ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር ውይይቶችን እንደሚያካሂድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ. በኖቬምበር 2023 ቼክ ሪፐብሊክን መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።
የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፊያላ እ.አ.አ. በኖቬምበር 2023 እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያን ዩሪችካ እ.አ.አ. ዴሴምበር 2024 በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል።