ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው - የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋትና የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሩ የአፍሪካ መገለጫ ጦርነትና ድርቅ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ጸጋና ኃብትም ጭምር በመሆኑ ይህንን ለማጉላት ኢዜአ ይዞት የተነሳው ሀሳብ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

በኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዛሬ ጎብኝቷል።


 

ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለልዑክ ቡድኑ ያደረገውን አቀባበል አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በሚዲያው ዘርፍ እያሳየ ያለው አስተዋጽኦና እድገት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተቋሙ ራዕዩን ለማሳካት የሚያግዝ ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጂ መታጠቁንና ሙያዊ ክህሎት የተላሰበ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት መኖሩን መገንዘባቸውንም ተናግረዋል።

የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ሥራዎቻቸውን በትጋት ለማከናወን ያላቸው ጉጉት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ተደራሽነቱን ለማስፋትና የአፍሪካ ድምጽ ለመሆን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።

አፍሪካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ለዓለም ማቅረብ የሚቻለው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የጀመረውን ስራ በመደገፍ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ መገለጫ ጦርነትና ድርቅ ብቻ አይደለም፤ ትልቅ ጸጋና ኃብትም ጭምር ነው ያሉት የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ በዚህ ረገድ ኢዜአ ይዞት የተነሳው ሀሳብ ግዙፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ የመረጃ የልብ ምት ለመሆን እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ይህ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ወዳጆች ብቻ አይደሉም፤ ድንበር ዘለል ግንኙነት ያላቸው የተዋለዱና የተሳሰሩ ህዝቦችም ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር ለጋራ ዓላማና ለአፍሪካዊ እሳቤዎች መጎልበት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

በኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ዋና ዳይሬክተር ኒኮዲሞስ ቦሬ የተመራ ልዑክ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው ሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ መታደሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም