ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለበልግ አብቃይ አካባቢዎች ምቹ የአየር ሁኔታ ይኖራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአብዛኞቹ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች አመቺ ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የካቲት ወር በመደበኛ ሁኔታ የበልግ ዝናብ የሚጀምርበት ጊዜ እንደሆነ ጠቅሷል።

በተለይም ከወሩ አጋማሽ በኋላ ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እየተጠናከሩ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ የደቡብ ምዕራብ፣ የደቡብ፣ የሰሜን ምሥራቅ፣ የምሥራቅ፣ የመካከለኛውና አጎራባች የስምጥ ሸለቆ ሥፍራዎች የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል፡፡

በመጪው የካቲት ወር የበልግ ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀስ በቀስ እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ እና ለዝናብ መኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ በትንበያ መረጃው ተጠቁሟል፡፡

ከእዚሁ ጋር ተያይዞ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በምሥራቅ፣ በመካከለኛውና አጎራባች የስምጥ ሸለቆ ሥፍራዎች ላይ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ነው የተባለው።

ይህም በልግ አብቃይ በሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የአፈር ውስጥ እርጥበትን እንደሚያሻሽል ተመላክቷል።

በዚህም የማሳ ዝግጅት ለማከናወንና የተለያዩ የበልግ ወቅት ሰብሎችን አስቀድሞ መዝራት የሚያስችል በመሆኑ አርሶ አደሮች እና የሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት አስፈላጊውን የዘር ግብዓት ከወዲሁ ማዘጋጀት እንዳለባቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታው ለቋሚ ተክሎች የውሃ አቅርቦት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ ለአርብቶ አደሮችና ለከፊል የአርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንጻር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።

በዚህም በባሮ አኮቦ፣ በኦሞ ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆ፣ በገናሌ ዳዋ፣ በላይኛው አዋሽ እንዲሁም በጥቂት ላይኛው ተከዜ እና የአፋር ደናክል ተፋሰሶች መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖራቸው ነው የተገለጸው፡፡

ይህ ሁኔታ ለገፀ ምድር ውሃ ሀብት መሻሻል አዎንታዊ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው የዝናብ ውኃ በማሰባሰብ እና በማከማቸት የውኃ ሀብትን የማሳድግ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በአንጻሩ አብዛኛው ዋቢ ሸበሌ፣ ኦጋዴን፣ አይሻ፣ መረብ ጋሽ፣ መካከለኛው እና ታችኛው አዋሽ፣ ዓባይ፣ ተከዜ እንዲሁም የታችኛው ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚኖራቸው ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም