ቀጥታ፡

ባለስልጣኑ ውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማስተዳደር ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

ባለስልጣኑ ስምምነት የተፈራረመው ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ነው።

ስምምነቱ የተቋማቱ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ማለዳ ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ፥ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ለዘላቂ ልማትና ብልፅግና ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ ውሃ አዘል መሬት መኖሩን ጠቅሰው፥ ይህም የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ያለውን ሚና ለማሳደግ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ አካባቢን እና የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

የውሃ አዘል መሬቶችን መጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተው፣ የተጀመሩ ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

የውሃ አዘል መሬቶች ለግብርና እና ቱሪዝም ልማት፣ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።

ይሁንና እነዚህን ውሃ አዘል ወይም ረግረጋማ መሬቶችን በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ካልተቻለ የመድረቅና የመጥፋት አደጋ ያጋጥማቸዋል ነው ያሉት።

ይህም በብዝሃ ህይወት መጥፋት ላይ አደጋ ከመፍጠር ባለፈ አካባቢ ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን አንስተዋል።

ባለስልጣኑ የውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማስተዳደር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ የተቀናጀና ውጤታማ የውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም