የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ አቋም መግለጫ አንኳር ሃሳቦች - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ አቋም መግለጫ አንኳር ሃሳቦች

ብልፅግና ፓርቲ ላለፉት ለሶስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በስኬት ማጠናቀቁን ገልጿል።
ፓርቲው ባለፉት ሶስት ዓመታት ሁለተናዊ ሀገራዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ባደረጋቸው ጥረቶች የተገኙ አስደማሚ ውጤቶችን ለማስቀጠል እና በቀጣይ በትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸውን ወሳኝ ነጥቦችን በተመለከተ ባለስምንት ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባዔውን አጠናቋል። የአቋም መግለጫ አንኳር ሀሳቦችን እንደሚከተለው በአጭሩ ቀንጭበን አቅርበናል።
*ጠንካራ ፓርቲ ግንባታን በተመለከተ፦
ባለፉት ሶስት ዓመታት ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት የተከናወኑ ስራዎች ፓርቲው ከዕድሜው የቀደመ የዕድገት ምዕራፍ ላይ እንዲገኝ አስችለዋል። ጠንካራ፤ ጤነኛና ውጤታማ ፓርቲ ለመገንባት ቋሚ ትግል እንደሚያሻ ተገንዝበናል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ የፖለቲካ ባህል በመገንባት ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ውጤት ተመዝግቧል።
ጉድለቶችን ለማረም አቅም ያለው፣ ሀገራዊ የመንግስት ኢኒሸቲቮችን በሃሳብ የሚመራ እና የህዝብን ንቅናቄዎች በብቃት የሚያስተባብር ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት የጋራ አቋም ወስደናል።
የአመራርና አባላትን አቅም በማሳደግ በአስተሳስብና በተግባር ብልፅግና የሆኑ፤ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በውጤታማነት እየፈጸሙ የህዝቡን ሕይወት የሚለውጡ፤ የጠንካራ ዲሲፕሊን እና የመልካም ስነ ምግባር መገለጫ የሆኑ፤ የኢትዮጵያን ህልም ዕውን የሚያደርጉ አመራርን አባላት ለማፈራት ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት የምንሰራ ይሆናል።
ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት እንዲቻል ዘመኑን ማላመድ የሚያስችሉ የሃሳብና የታሪክ ውህደት በመፍጠር፣ መዋቅራዊ ልህቀት በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ስክነትን ዕውን በማድረግ እና የውጤት ዘላቂነትን በቁርጠኝነት ለመፈፀም ዳግም ቃል እንገባለን።
*የጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት ግንባታን በተመለከተ፦
የሀገረ መንግስት ቅቡልነት ለማረጋገጥ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን በማብዛት ለጠንካራ የሀገረ መንግስት እና የደሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ እንሰራለን።
የተጀመረውን የተቋማት ረፎረም በማጠናከር ተቋማቱ ነጻነታቸው ተጠብቆ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማስጠበቅ አስተማማኝና ነጻነታቸው የተጠበቁ፣ የሀገር ጋሻ እና መከታ ሆነው በዘላቂነት እንዲገነቡ እንደግፋለን።
የህዝቡን ፍትህ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ የፍትህ ስርዓትን የማዘመን፣ ባለሙያዎችን የማብቃት፣ የዳኝነት አገልግሎት ነጻነትን እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንታገላለን።
*ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥን በተመለከተ፦
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረገጋጥ በአጭር ጊዜ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ማየት እንሻለን። ህልማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና የተረጋገጠባትና አፍሪካዊት የብልጸግና ተምሳሌት የሆነች እና ዓለም አቀፋዊ የተፅዕኖ አድማሷ የሰፋ ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ነው።
ለኢኮኖሚ ብልፅግና ግቦች ስኬት በጋራ በመቆም ኢኮኖሚው ነባር አቅሞችን የሚያጠናክር፣ ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚሸጋገር እና ወደ መጪው የፈጠራ ዘመን የሚያስፈነጥር ይሆን ዘንድ ለመታገል ወስነናል።
ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ስርዓት በመፍጠር ኢኮኖሚውን ከብድር ጫና የሚያላቅቅ አቅጣጫ አስቀምጠናል። ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማጎልበት የህዝቡን አዳጊ የልማት ፍላጎት ለመመለስ እንሰራለን። አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማስተባበር አቋም ወስደናል።
በቀጣይ ሶስት ዓመታት የተቃና የኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ዲጂታል ኢኮኖሚ ተደምሮ መዋቅራዊ ሸግግር የኢኮኖሚ ሽግግር ያመጣ ዘንድ አበክረን እንሰራለን።
*ማህበራዊ ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ፦
ማህበረሰቡ ሁለተናዊ ብልፅግና ተረጋገጦለት ሁለንተናዊ ክብሩ እንዲጠበቅ አካታቸ ማህበራዊ ልማት ዕውን እንዲሆን እንሰራለን።
ትውልዱ ጥራት ባለው ትምህርት እንዲያገኝ እና የወንድማማችነት፣ የመቻቻል፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እና አርበኝነት እሴቶች እንዲማር የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ።
በጤና መድህን አገልግሎት፣ ጤና ተቋማት ተደራሽነት እና ጥራት የማሻሻል እንዲሁም አካታች የሆኑ ሰው ተኮር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
የተጀመሩ የማህበራዊ ልማት ስራዎቻችን ሁለንተናዊ ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ አጠናክረን እንቀጥላለን።
*ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ገዥ ትርክት ግንባታን በተመለተከ፦
ሕብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጠናከር ከነጣጣይ ትርክቶች ይልቅ አስተሳሳሪ ትርክቶች አሸናፊ ሆነው ወጥተው ገዥ ትርክት እንዲሆኑ እንሰራለን።
ለሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ገዥ ትርክት ለማስረጽም በመላ ሀገሪቷ በተለያዩ አማራጮች ህዝባዊ ውይይቶች ይደረጋሉ።
የሃሳብ ነጻነት መከበር እንደተጠበቀ ሆኖ ማህበራዊ ሚዲያ ከአፍራሽ ተልዕኮ ይልቅ ለገዥ ትርክት እና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ እንዲሁም የኢትዮጵያን ዕውነት ለመግለጥ እንዲውል አበክረን እንስራለን።
*የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ሪፈሮምን በተመለከተ፦
የሀገራችን ሲቪል ሰርቪስ ለማሻሻል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተሳሰረና ከብልሹ አሰራርና ሌብነት የተላቀቀ ሲቪል ሰርቪስ ስርዓት ለመገንባት ገቢር ነበብ ሪፎርም በትኩረት እየተሰራ ነው።
በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ብልሹ አሰራሮች ህዝብ ለእንግልትና ለሮሮ እየዳረጉ በመሆ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፍትህ ስርዓት ሪፎርም በማጠናከር የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር ጠንከራ አቋም ወስደናል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እና ገቢር ነበብ ሪፎርም በማከናወን ቅሬታ ምንጭ በሆኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
*ሀገራዊ ክብርና አንድነትን የሚያጠናክሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች በተመለከተ፦
ባለፉት ዓመታት የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ስራዎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ያስቀደሙ፣ የመሪና የፓርቲ አቅም ያሳዩ ሲሆኑ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ የዲፕሎማሲ ትግሉ ሁነኛ ማሳያ ነው።
የትውልድ ጥያቄ የነበረው የባሕር በር አጀንዳ በዓለም አደባባይ ተገቢ ትኩረት እንዲያገኝ ሆኗል።
ዲፕሎማሲያችን ከመሽርመም ተላቆ ብሔራዊ ጥቅምን፣ መርህና ዕውነትን እንዲሁም የዜጎችን ክብር መሰረት ያደረገ አቅጣጫ ይዟል።
ዘላቂ የባሕር በር የማገኘት ፍላጎት በሰላማዊና በዲፕሎመሲያዊ መንገድ ምላሸ እንዲያገኝ በተገኘው የዓለም መድረከ ሁሉ ለመታገል ቆርጠን መነሳታችንን እናረጋግጣለን።
*ሀገራዊ ምክክር በተመለከተ፦
ዘላቂ ሰላም የሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ አካታች ሀገራዊ ምክከር ተደርጎ የኢትዮጵያ የዘመናት የችግር ስንክሳር በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝ የተጀመረውን ጥረት እንደግፋለን።
የተጀመረው የሽግግር ፍትህ ሂደት ተግባራዊ እንዲሆን የተጣለብንን ሃላፊነት በብቃት ለማስፈጸም እንሰራለን።
ከታጣቂ ሃይሎች ጋር የሚደረግ ውይይትና ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ግጭት እንዲቀር ተጨማሪ አቅጣጫ አስቀምጠናል። ሁሉም የፓርቲው አመራርና አባላት ለሰላም ግንባታ እንዲሰራ ተስማምተናል።
የጉባዔውን ውሳኔዎችን በመተግበር ሀገራዊ ሰላም ለማረገጋጥና ህብረ ብሄራዊ አድንድነታችንን አጠናክረን ለማስቀጠል ሁላችንም በአንድነትና በጽናት እንቆማለን።
ለጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔዎች ተግባራዊነትም ተግተን እንሰራለን።