በተጠባቂው ጨዋታ አርሰናል ማንችስተር ሲቲን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ አርሰናል ማንችስተር ሲቲን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2017 (ኢዜአ) ፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሃ ግብር አርሰናል ማንችስተር ሲቲን 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ማርቲን አዴጋርድ፣ ቶማስ ፓርቴይ፣ ማይልስ ሉዊስ-ስኬሊ ፣ካይ ሃቫርትዝ እና ኢታን ንዋኔሪ የማሸነፊያ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አርሊንግ ሃላንድ ለማንችስተር ሲቲ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ነጥቡን ወደ 50 ከፍ አድርጓል።
ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ አድርጓል።
ማንችስተር ሲቲ በ41 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዟል።
ሊቨርፑል በ56 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።