ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዙር ዓለም አቀፍ የቁርአንና የአዛን ውደድር ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዙር ዓለም አቀፍ የቁርአንና አዛን ውደድር በወንዶች አዛን እና በሴቶች የቁርአን ሂፍዝ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች።

ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችው የ2017 ዓለም አቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር ማጣሪያ ባለፉት ቀናት ዓለም አቀፍ የቁርአን ዳኞች በተገኙበት ሲካሔድ ቆይቷል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ አሸናፊዎች የተለዩበት የማጠቃለያ ውድድር እና የሽልማት ስነ-ስርዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከናውኗል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋን ጨምሮ፣ ዓለም አቀፍ ዳኞች፣ ከሀገራት የመጡ ተወዳዳሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በፍጻሜው ኢትዮጵያ በሴቶች የቁርአን ሂፍዝ ዘርፍ በቀመሪያ ወልዩ ሙሀመድ አማካኝነት ሶስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

እንዲሁም በወንዶች አዛን ደግሞ በአደም ጅብሪል አማካኝነት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

በውድድሩ በወንዶች በቁርአን ሂፍዝ ሊቢያ አንደኛ፤ በወንዶች አዛን ኢንዶኔዢያ አንደኛ፤ በቁርአን ሂፍዝ ሴቶች የመን አንደኛ እንዲሁም በወንዶች ቁርአን ቲላዋ (ድምጽ ማውጣት) ግብጽ የአንደኝነት ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል።

ለአሸናፊዎቹ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

በሽልማት ስነ ስርዓቱ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ፤ ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ውድድሩ በስኬት የተካሄደው በሀገራችን ሰላም በመኖሩ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ለዓለም ዘላቂ ሰላም ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በውድድሩ የተሳተፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች የመስህብ ስፍራዎችን የጎበኙ ሲሆን ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የበላይ ጠባቂነትና በዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር አማካኝነት በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር ላይ 60 ሀገራት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም