አዳዲስ የስፖርት አይነቶችን በማስፋፋት ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እየተሰራ ነው - ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ የስፖርት አይነቶችን በማስፋፋት ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እየተሰራ ነው - ፌዴሬሽኑ
ደብረ ብርሀን፤ ጥር 25/2017(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ አዳዲስ የስፖርት አይነቶችን በማስፋፋት ዘርፉን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እንደሚሰራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
በደብረ ብርሀን ከተማ የፉትሳል ስፖርት የአሰልጣኞች ስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የፉትሳል ስፖርት ከእግር ኳስ ጨዎታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው፣ በውስን ስፍራና አነስተኛ የሰው ቁጥር የሚካሄድ ስፖርት መሆኑን ተናግረዋል።
በደብረ ብርሀን ከተማ የተጀመረውን የፉትሳል ስፖርት እንደ ሀገር ለማጠናከር ስፖርቱን በሌሎች ክልሎችም ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ አዳዲስ የስፖርት አይነቶችን በማስፋት ዘርፉን ለቱሪዝም ልማት ምቹ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ነው የገለጹት።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው፤ ከሀገራዊ ለውጡ ጀምሮ ስፖርትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለዘርፉ እድገት አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም በከተማው እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ብቃት ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አውራሪስ አረጋ በበኩላቸው፤ የፉትሳል ስፖርትን ለማልማት ይሰራል ብለዋል።
ስፖርቱን በማስፋፋት ብቁ ተወዳዳሪዎችን ከማፍራት ባለፈ ለቱሪዝም ልማት ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ፉትሳል ስፖርት ዘንድሮ በደብረ ብርሀን እግር ኳስ ክለብ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የደብረ ብርሀን እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ አቶ ሰለሞን አየለ ናቸው።
ከስፖርቱ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለው ሙያዊ ስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በከተማዋ በፉትሳል ስፖርት 120 ታዳጊዎች ታቅፈው ስለጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙም አመልክትዋል።
ስልጠናውን እየወሰዱ ካሉ አሰልጣኞች መካከል ኤልሳ ሀይለመስቀል በበኩሏ፤ አሰዴ ካታላን ባርሴሎና የትምህርትና የስፖርት ልማት ድርጅት የፉትሳል ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ እንዲያድግ እያደረገ ያለው ድጋፍ ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግራለች።
የአሰዴ ካታላን ባርሴሎና የትምህርትና የስፖርት ልማት ድርጅት ፕሬዚዳንት ዣቪየር እስቲባ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚደረገው የትጥቅና የስልጠና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት 100 የፉትሳል የአሰልጣኞች ስልጠና በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የሚሰጥ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የትጥቅ ድጋፍ ተደርጓል።
ስልጠናው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከደብረ ብርሀን ከተማ እግር ኳስ ክለብ፣ ከአሰዴ ካታላን ባርሴሎና የትምህርትና የስፖርት ልማት ድርጅትና ሌሎች አካላት ጋር በመተባባር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።