ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተመለከትነው የልማት ስራ እጅግ አስደናቂ ነው - የእህት ፓርቲ ተወካዮች

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የተመለከቱት የልማት ስራ እጅግ አስደናቂ መሆኑን የደቡብ ሱዳንና የናይጀሪያ እህት ፓርቲ ተወካዮች ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባዔ እየታደሙ የሚገኙ የእህት ፓርቲዎች አመራሮችና ተወካዮች በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡


 

የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ(SPLM) ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም ቦዝ ከረጅም ጊዜ በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደነበሩና ኢትዮጵያን በደንብ እንደሚያውቋት አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ በሀገሪቱ የሚታይ ለውጥ እንዳልነበር ጠቅሰው ከረጅም ቆይታ በኋላ ባለፈው ህዳር የደቡብ ሱዳንን ልዑክ በመምራት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከተማዋን ለማስታወስ እስከሚቸግራቸው ድረስ ከፍተኛና አስደናቂ ለውጥ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የማውቃት አዲስ አበባ እስከማትመስል ድረስ በርካታ ለውጦችን አይቻለሁ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።


 

የመሰረተ ልማት ግንባታው መንገድ፣ ድልድይ እንዲሁም የባቡር መስመር ግንባታዎችን ማካተቱን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቤተ መንግስት በነበራቸው የጉብኝት ቆይታም እዚህ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ በቤተመንግስት በኩል ማለፍ በራሱ ከባድ ነበር ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ይህ ቤተ መንግስት አሁን የአንድነት ፓርክ ተብሎ ተሰይሞ ስመለከትው ተደንቂያለሁ፣ ህፃናት በግቢው ውስጥ ሲጫወቱ ተመልክቻለሁ፣ ጎብኚዎችም ዘና ብለው በግቢው ሲዘዋወሩ አይቻለሁ፣ ይህ በራሱ ድንቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሰሩት ስራ ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው ያሉት ሀላፊው፤ የተባበረች አፍሪካን እውን ለማድረግ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካን ፍላጎት በአፍሪካ ጥሬ ሃብት ማስጠበቅ እንችላለን፤ አሁን ጊዜው እንደ አፍሪካ ከፍ ብለን ልንታይበት የሚገባ ወቅት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡


 

የናይጄሪያው ኤፒሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አልሀጅ አሊቡካር ዳሎሪ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን በመግለጽ ባዩት ነገር በጣም መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ ታሪካዊ መሆኗን መመልከታቸውን ጠቅሰው የተመለከቱት የልማት ስራ አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት መሪ ናት፣ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ መሪነት ይህንኑ መሪነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምናለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣይ ስራዎቹ ስኬታማ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸው፤ ህዝቡም መንግስት በጀመረው የእድገት ጉዞ ትብብሩን በማጠናከር ወደ ስኬት ማምራት እንደሚችል አምናለሁ ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷን በተግባር የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነች ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ጊዜያት አሁን ካየሁት የበለጠ ጎልታ እንደምትታይ አልጠራጠርም፤ እንደ ፓርቲ አፍሪካን በጋራ ለማሳደግ በትብብር መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም