ቀጥታ፡

ብሄራዊ ቤተ መንግስት እጅግ አስደናቂ እና የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል በሚገባ ሰንዶ የያዘ ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 25/2017(ኢዜአ)፦ብሄራዊ ቤተ መንግስት እጅግ አስደናቂ እና የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል በሚገባ ሰንዶ የያዘ ነው ሲሉ የዚምባቡዌው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የብሔራዊ ውጭ ግንኙነት ዋና ጸሃፊ ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ ገለጹ።

በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ እየታደሙ የሚገኙ የወዳጅ ሀገራት እህት ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች የአንድነት ፓርክና ብሄራዊ ቤተመንግስት ሙዚየምን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

የዚምባቡዌው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ የብሔራዊ ውጭ ግንኙነት ዋና ጸሃፊ ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ በአንድነት ፓርክና በብሄራዊ ቤተመንግስት የተመለከቷቸው ሃብቶች በጣም የሚያምሩና የሚደነቁ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በመንገድ፣ ህንፃዎች፣ ድልድዮች እና በባቡር መስመሮች ጉልህና የሚደነቅ የመሰረተ ልማት ለውጦች መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ዕድሳት ተደርጎለት ለህዝብ ክፍት የተደረገው ብሄራዊ ቤተ መንግስት እጅግ አስደናቂ እና የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል በሚገባ ሰንዶ የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዋና ጸሀፊው አክለውም ፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዘመናት የቆየ ግንኙነት መኖሩን ጠቁመው፥ ኢትዮጵያ ለዚምባብዌ ነጻ መውጣት ወሳኝ ድጋፍ ማድርጓን አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ የተመለከቱትን እጅግ አስደናቂ ልማት በተለይም የከተማዋን የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ጽዳት አድንቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በሀገሪቷ በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ በማድረጉ ያላቸውን አድናቆት ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት መሆኗን የሚመሰክሩ አስደናቂ ለውጦችን እያሳየች መሆኗን ገልጸዋል።

ዛኑ-ፒኤፍ እና የብልጽግና ፓርቲ የትብብር ስምምነቶችን ለመፈራረም በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የካዛኪስታን አማናት ፓርቲ አባልና እና የሀገሪቱ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት አባል ሳማት ኑር ታተዛ በበኩላቸው፥ አዲስ አበባ ለኑሮ የምትመች ህዝቦቿም እንግዳ ተቀባይ ናቸው ብለዋል።

እንደ አገር በፓርቲዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ትሩፋቶች አፍሪካ በልማት ጎዳና መሆኗን የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመሪነቷ ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን ያሳያል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እድገት የሚታይና የሚጨበጥ መሆኑን የገለጹት የምክር ቤት አባሉ፤ ለውጡ ለአፍሪካ ብሎም ለማዕከላዊ እስያ አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት በሀገሪቷ የሚታዩ ለውጦች ማስመዝገቡን ገልጸው፥ የፓርቲ ለፓርቲ ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም