በሲዳማ ክልል የተከናወነ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ሥራ የግብርና ምርታማነትና የደን ሽፋንን አሳድጎታል--ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የተከናወነ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ሥራ የግብርና ምርታማነትና የደን ሽፋንን አሳድጎታል--ቢሮው
ሀዋሳ፤ ጥር 25/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የተፋሰስና የአረንጓዴ ልማት ሥራ የግብርና ምርታማነትና የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ዘንድሮም ቀደም ሲል በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተገኘውን ውጤት ለማጠናከርና የሀዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል ለሚያስችሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ትኩረት መስጠቱም ተመላክቷል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስና የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎች ክልላዊ የደን ሽፋንና የግብርና ምርታማነት እያደገ መጥቷል።
በልማት ሥራው የደን ሽፋንን ከአስር ዓመት በፊት ከነበረበት 13 በመቶ በአሁኑ ውቅት ወደ 26 በመቶ ለማሳደግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የመሬት ለምነትን ከመመለስ ባለፈ የጠፉ ምንጮች እንዲያገግሙ እንዲሁም ምርታማነት እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
የቢሮው ምክትልና የተፈጥሮና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል።
እስካሁን በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች የተገኘው ውጤት ምርታማነትን በማሳዳግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቦርቻ ወረዳ የአልዳ ዴላ እና የአቦና ጭሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘካሪያስ ናማሮ እና አርሶ አደር አሸናፊ ግርማ የተፋሰስ ልማት ሥራው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘላቸው መሆኑ ተናግረዋል።
በልማቱ በክረምት ወቅት የጎርፍ ተጋላጭነታቸው ከመቀነሱ ባለፈ የተራቆተ መሬት መልሶ ማገገሙንና ለእንስሳትም የመኖ ሳር ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ልማቱ ድርቅን በመከላከል የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እያገዛቸው በመሆኑን ዘንድሮም አጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የተናገሩት።
ሌላኛዋ የአልዳ ዴላ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ቡኣ በበኩላቸው የሚኖሩበት ቀበሌ ገላጣ በመሆኑ በጎርፍና በነፋስ በተሸረሸረ መሬት ምርታማነታቸው በእጅጉ ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በተፋሰስ ስራ ጠረጴዛማ እርከን ጨምሮ ውሃን ለመያዝ የሚያግዙ የልማት ሥራዎች በመሰራታቸው ምርታማነታቸውን ለማሳደግና የእንስሳት መኖ ለማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።
በወረዳው ከ5 ሺህ 700 ሄክታር በላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የወረዳው እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በወረዳው በተሰራ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የመሬት ለምነት መመለሱንና ለኑሮ ተስማሚ አየር ሁኔታ መፈጠሩን አስታውሰዋል።
ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የሀዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል በወረዳው ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች የተፋሰስ ልማት ሥራው መጠናከሩን ገልጸዋል።
በክልሉ ከጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይና ህብረተሰቡን በነቂስ ያሳተፈ የተፋሰስ ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው።