ቀጥታ፡

ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን በፕሪሚየር ሊጉ ለ49ኛ ጊዜ የሚያገናኘው የደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሃ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በተመልካቾች በጉጉት ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን 15 ጨዋታዎችን አድርጎ 8 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ተሸንፎ 4 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹ 20 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 13 ግቦችን አስተናግዶ በ28 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 6 ጊዜ ድል ሲቀናው 5 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዶ 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በ15ቱ ጨዋታዎች 15 ጎሎች ሲያገባ 11 ግቦች ተቆጥረውበት በ22 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ49ኛ ጊዜ ነው።

ክለቦቹ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 48 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ

ኢትዮጵያ ቡና 8 ጊዜ አሸንፎ 19 ጊዜ ደግሞ በአቻ ተለያይተዋል።

በ48ቱ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 63 ግቦችን ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ ቡና 32 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋንጫ ተፎካካሪነቱ ለመቀጠል ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት የሚያደርጉት በመሆኑ የዛሬ ጨዋታቸውን ይበልጥ ተጠባቂ ያደርገዋል።

በ18ኛ ሳምንት ሌላኛው መርሃ ግብር ሲዳማ ቡና ከስሑል ሽሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሲዳማ ቡና በ19 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ሲይዝ ስሑል ሽሬ በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የ18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ እና መቻል የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው።

ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በ32 ነጥብ ሲመራ በአንጻሩ አዳማ ከተማ፣ ሃዋሳ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ ሰባት ጎሎች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም