አርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ መርሃ ግብር 

አዲስ አበባ ፤ጥር 25 /2017 (ኢዜአ):-በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ አርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል። 

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ክለቦች እስከ አሁን በሁሉም ውድድሮች 212 ጊዜ ተገናኝተዋል።

አርሰናል 99 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 65 ጊዜ ድል ቀንቶታል።

48 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታዎቹ 592 ግቦች ከመረብ ላይ አርፈዋል። 

በየጨዋታዎቹ በአማካይ 2 ነጥብ 7 ጎሎች ይቆጠራሉ ማለት ነው። 

አርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 50 ጊዜ ተገናኝተዋል። አርሰናል 23 ጊዜ ሲያሸንፍ ማንችስተር ሲቲ 17 ጊዜ ድል ቀንቶታል።

10 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። 
አርሰናል በጨዋታዎቹ 71 ጎሎችን ሲያስቆጥር ማንችስተር ሲቲ 64 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

አርሰናል በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች 23 ጨዋታዎች 13 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 8 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ 44 ጎሎቹን ሲያስቆጥር 21 ግቦችን አስተናግዷል። 

አርሰናል በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንችስተር ሲቲ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 23 ጨዋታዎች 12 ጊዜ ሲያሸንፍ 6 ጊዜ ተሸንፏል። 5 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 

ቡድኑ 47 ጎሎችን ሲያስቆጥር 30 ጎሎችን አስተናግዷል። ሰማያዊዎቹ በ41 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ለአርሰናል በዋንጫ ፉክክር ጉዞው ለመቀጠል ማንችስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመሳተፍ እድሉን ለማስፋት ለያዘው ውጥን የዛሬው ጨዋታ እጅጉን ወሳኝ የሚባል ነው።

የ42 ዓመቴ ስፔናዊ የአርሰናል አሰልጣኝ ከጨዋታው በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከማንችስተር ሲቲ ጋር የምናደርገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው፤ በዋንጫ ፉክክሩ ለምናደርገው ጉዞ ትላልቅ ቡድኖችን ማሸነፍ ትልቅ ተነሳሽነት ይፈጥራል ሲል ገልጿል።

ሁለቱ ቡድኖች በቅርብ ዓመታት ዋንጫ ለማንሳት እያደረጉት ያለው ፉክክር ጨዋታቸውን ይበልጥ ተጠባቂ እንደሚያደርገው ተናግሯል።  

የ54 ዓመቱ ስፔናዊ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ የቁርሾ ጨዋታ እንዳልሆነ በመግለጽ የጋዜጠኞችን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

እኔ እና አርቴታ ያለን ግንኙነት የተለየ ነው፤ አንዳችን ለአንዳችን አክብሮት አለን ሲል ተናግሯል።

ስፔናዊው የአርሰናል ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ በጡንቻ ጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ላይ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። 

በማንችስተር ሲቲ በኩል በጉዳት ላይ ካሉ ተጫዋቾች መካከል ለዛሬው ጨዋታ የሚደርስ እንደሌለ ጋርዲዮላ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አንስተዋል። 

የ42 ዓመቱ እንግሊዛዊ ፒተር ባንክስ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል። 

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረገ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታ የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ቦርንማውዝን ከሜዳው ውጪ በመሐመድ ሳላህ ግቦች 2 ለ 0 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 56 ከፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም