ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያዎች ተከላ ሊያከናውን ነው

አሶሳ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያ ተከላ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 11 ወረዳዎች ላይ ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገበያ ጣቢያዎች ተከላ ለማከናወን ውይይት አካሂዷል።


 

በኢንስቲትዩቱ የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት በየጊዜው የሚከሰተውን የአየር ፀባይ ለውጥ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነው።

በዚህም ከቆላማ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በክልሉ 11 ወረዳዎች ላይ ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያ ተከላ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ጣቢያዎቹ ታማኝና ትክክለኛ መረጃ በመሰብሰብ ለግብርና ስራ በሳይንስ የተደገፈ መረጃ ለመስጠት ያግዛሉ ብለዋል።


 

ከዚህም በተጨማሪ የአጭር እና የረጅም ጊዜ የአየር ትንበያ መረጃ በመስጠት የአካባቢው ማህበረሰብ ለግብርና ስራው ዝግጅት እንዲያደረግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ በመስጠት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕከል ጊዜያዊ ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ሰለሞን በበኩላቸው የሚተከሉት ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያዎች መረጃን በፍጥነት እና በጥራት ለመሰብሰብ ያግዛሉ ብለዋል።

ማዕከሉ በክልሉ የሚሰበስበው የትንበያ መረጃ የተቀላጠፈ እና በዲጂታል መልኩ ለመመዝገብ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም