በትናንት ታሪኳ ለአፍሪካ ነጻነት ውለታዋ፤ ዛሬ ደግሞ በብልፅግና ጉዞዋ ለኢትዮጵያ አድናቆትን የቸሩት የዚምባቡዌው አንጋፋ ፖለቲከኛ- ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ - ኢዜአ አማርኛ
በትናንት ታሪኳ ለአፍሪካ ነጻነት ውለታዋ፤ ዛሬ ደግሞ በብልፅግና ጉዞዋ ለኢትዮጵያ አድናቆትን የቸሩት የዚምባቡዌው አንጋፋ ፖለቲከኛ- ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ
የ79 ዓመቱ ዕድሜ ባለጸጋ ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ በትውልድ ሀገራቸው ዚምባብዌ ጉምቱ ፖለቲከኛና የዲፕሎማሲ ሰው ናቸው።
በ1940ዎቹ አጋማሽ በቅኝ ገዥዎች አስተዳደር ዘመን የተወለዱት ሙቤንጌግዊ ግዛት ዘመን የተወለዱት የፖለቲካ ትግል የጀመሩት በሀገረ አውስትራሊያ የውጭ ሀገር ተማሪ እያሉ ነበር።
ይሄውም በፈረንጆቹ 1960ዎቹ አንጋፋውን የዚምባብዌ የአፍሪካ ብሔራዊ አንድነት አርበኞች ግንባር ወይም የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ(Zimbabwe African National Union Patriotic Front- Zanu PF) የተማሪዎች ተወካይ እንዲሁም የኤዥያ ቀጣና ተወካይ ሆነው ነበር ንቅናቄውን የተቀላቀሉት።
ሀገራቸው ከቅኝ ግዛት ነጻ እስከትወጣ ድረስ በተለያዩ ሀገራት የፖለቲካ ትግል ሲያደርጉ ቆይተው ድሕረ ነጻነት በዛኑ ፒኤፍ ማዕከላዊ ኮሚቴነትና በሌሎች የተለያዩ ከፍተኛ የፓርቲ አመራርነት ደረጃ አገልግለዋል። ዛሬም እያገለገሉ ነው።

ሙቤንጌግዊ ከዘመነ ሮበርት ሙጋቤ ጀምሮ በዚምባብዌ የዲፕሎማሲ ታሪክ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት እና በተባበሩት መንግስታት ውስጥ ሀገራቸውን ወክለው ለረጂም ጊዜ በዲፕሎማትነት አገልግለዋል።
በሚኒስትርነት ደረጃም በውጭ ጉዳይ፣ በማክሮ ኢኮኖሚክ ፕላኒንግና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ በውሃ ሀብትና ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በቤቶች ልማትና በሌሎች የሚኒስቴር ተቋማት ሚኒስትር ሆነው መንግስታዊ ሃላፊነቶች ተወጥተዋል። በዚምባብዌ ፓርላማ አባልነትና የቋሚ ኮሚቴዎች ሃላፊነትም እንዲሁ።
ዛሬም በሀገሪቷ ገዥ ፓርቲ በሆነው በዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዋና ጸሃፊ ሲሆኑ የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ እንደሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያዊያን የአርበኝነት መንፈስ ለፀረ ቅኝ ግዛትና አፓርታይድ ስርዓት ትግል እንዲቀጣጠል አድርጓል-
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል።
ከእንግዶቹ መካከልም የዚምባቡዌው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ዋና ጸሃፊ ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ ይገኙበታል።
በአድዋ መታሰቢያ በተደረገው የጉባዔው መክፈቻ ላይ ተገኝተው የሀገሪቷን ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና የፓርቲያቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ብቸኛዋ ቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች ሀገር በመሆኗ ትልቅ አድናቆትና ዕውቅና ይቸራታል ብለዋል።
የኢትዮጵያዊያን የአርበኝነት መንፈስ ለፀረ ቅኝ ግዛትና አፓርታይድ ስርዓት ትግል እንዲቀጣጠል ቁልፍ አበርክቶ እንደነበረው ጠቅሰዋል።

አብዛኛው የአፍሪካ ነጻነት ትግሎች በኢትዮጵያዊያና በቆራጥ ኢትዮጵያዊያን ቁሳዊ፣ ሞራላዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎች የታጀቡ ነበሩ ብለዋል።
የዚምባብዌ ነጻነት ሃይሎች ታሪክም ከዚህ የተለዩ አይደለም ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠናዎች እንዲሁም የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳገኙ አውስተዋል። ዚምባብዌ ቅኝ ገዥዎችን ታግላ ድል ስትቀዳጅ የኢትዮጵያና የህዝቧን ውለታ እንደማትረሳ በመጠቆም።
ፓርቲያቸው በብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ሲጋበዝ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት የነበራትን ቁልፍ ሚና ዕውቅና በመስጠት የእንኳን ደስ አላችሁ ደስታውን ያበስራል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ብልፅግና በሀገር በቀል እሳቤ ሀገር ለመለወጥ የተነሳ ፓርቲ መሆኑን መጥቀሳቸውን አድንቀው፤ ሀገር የሚለወጠው በሀገሬው ሀሳብና በሀገሬው ሰው ሲመራ ነው የሚለውን የሀገራቸው ስነ ቃል አጣቅሰው የሀሳቡ ተጋሪ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በታሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ለማምጣት በመታተር በአጭር ጊዜ ያሳካቸውን ድሎች አድንቀዋል።
እስካዛሬ በርካታ ጉባዔዎችን ብታደምም እንደ ብልፅግና ፓርቲ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በማሳተፍ አካታችንቱን ያሳዬ ፓርቲ አላየሁም ሲሉ ለዲሞክራሲ ምህዳር መስፋት የተደረገውን ጥረት አወድሰዋል።
የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ በእርግጥም አስደናቂና የማይተማን ሲሉ አሞካሽተውታል። እንዴትስ ይህ ሁሉ ስኬት መጣ ሲሉ ተጠየቅ ሰንዝረዋል።
በአዲስ አባባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች እኔን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የውጭ ዜጋ ያማለሉ ተጨባጭ የለውጥ ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
በርግጥም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የሆነችውም በአጋጣሚ አይደለም፤ አዲስ አበባ ሁላችን የምንመካባት ውብ ከተማችን ናት ሲሉም በኩራት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያና በዚምባብዌ መንግስታት መካከል የሁለትዮሽ ዕውነተኛ ትብብር እንዲጎለበት እንዲሁም ከብልፅግና ፓርቲ ጋር የሚደረጉ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች ከምንጊዜውም በተሻለ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ አረጋግጠዋል።