ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ምንጊዜም የምስራቅ አፍሪካ ምሰሶ ነች - ኢልያስ ሙሳ ዳዋሌ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የሰላምና ደህንነት ምሰሶ መሆኗን የጅቡቲው ፒፕልስ ራሊ ፎር ፕሮግረስ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ኢልያስ ሙሳ ዳዋሌ ገለጹ።

"ከቃል እስከ ባህል" ከዛሬ ጥር 23 እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት መካሄድ ጀምሯል።

በሥነ-ሥርዓቱ የተገኙት የጅቡቲው ፒፕልስ ራሊ ፎር ፕሮግረስ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ኢልያስ ሙሳ ዳዋሌ፤ የዓድዋ መታሰቢያ ያረፈበት ስፍራ ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር የአፍሪካዊያን የጠንካራ አንድነትና የድል ምልክት ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባና በመላ ኢትዮጵያ በተወሰደው ስር-ነቀል ለውጥ በከተማና ገጠር በመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ የተመዘገበው ስኬትም እውቅና የሚቸረው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ እንደ ስሟ የበለጠ አዲስ ነች ዛሬ ያሉት ዋና ጸኃፊው፤ ኢትዮጵያ በወሰደችው ቆራጥ አመራር በግብርና መስክ አርዓያ መሆን የቻለችበትን ፈጣን ስኬት አስመዝግባለች ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገትም ባለ ራዕይ አመራር መኖሩን በተግባር ያስመሰከረ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ተከስቶ የነበረውን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተወሰደው ድፍረትና ጥበብ የተሞላበት መፍትሔም ክብር እንደሚሰጠው አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባትና አንድነት ያሳየችው ቁርጠኝነትም መፃዒ ተስፋ በማለምለም ብልጽግናን እውን ማድረግ የምትችል ሀገር መፍጠር እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵና የሶማሊያ የወንድማማች ግንኙነት ወደቀደመ ሁኔታው መመለስም ቀጣናዊ ሰላምና አንድነትን ለማጎልበት የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የሀገራቱን ወዳጅነት ለመመለስ የተርኪዬ መንግስት ያበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦም ምስጋና የሚቸረው መሆኑን አስታውሰዋል።

በማይገመተው ዓለም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትና ጸጥታ ስጋት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ብክለት ምላሽ ለመስጠት በጥልቅ መሰረት የተገነባ ትብብርን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ቀጣናዊ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባትም ቅንጦት ሳይሆን አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ምንጊዜም የምስራቅ አፍሪካ ምሰሶ ነች ያሉት ኃላፊው፤ ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ከለላ እና የኢኮኖሚ ውህደት አጋር ነች ብለዋል።

በቀጣናውም በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለኢኮኖሚ ሽግግር ያላትን ገንቢ ሚና አጠናክራ መቀጠል እንደሚኖርባት ተናግረዋል።

ለዚህም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት፣ መሪዎችና ህዝቦች መካከል ቀጣይነት ያለው የመተማመን መንፈስ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የጅቡቲ ህዝብና መንግስትም ለብልጽግና ፓርቲ ራዕይ እውን መሆን የሚያደርገውን ትብብርና አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ዕርቅና መተማመን የምትፈጥርበት ሀገር በቀል እሴት ያላት ሀገር መሆኗ ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶቿ መገለጫ መሆናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጉልህ ፋይዳ አንዳለው አስገንዝብዋል።

በጉባኤው ላይ ከ1 ሺህ 700 በላይ የፓርቲው አመራር አባላት፣ የአፍሪካ፣ የብሪክስ አባል ሀገራትና የሌሎች ዓለም ሀገራት እህት ፓርቲ፣ የዓለም አቀፍ አጋር ድርጅት የስራ ኃላፊዎች፣ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም