ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት እውን እንዲሆንና የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ምክር ቤቱ እየሰራ ነው - የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት እውን እንዲሆንና የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የተገኙት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ፤ ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱ በሀገሪቱ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት እውን እንዲሆንና የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ ለረጅም ዘመናት የነበውን የመጠፋፋት ፖለቲካ ባህል በመቀየር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መተባበር፣ መተራረምና መፎካከርን እውን ማድረግ ያስቻለ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠሩንም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መጋቢት 5 ቀን 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመው ያቋቋሙትና በሀገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ባሳዩት ቁርጠኝነት ምክር ቤቱ የሚመራበትን መመሪያና ደንብ ማጽደቅና አሰራር እና አደረጃጀቱን እስከ ወረዳ ማዋቀር መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

አመራሮቹም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲመረጡ በማድረግ የሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ መድረክ ልምምድ እውን እንዲሆን መስራት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ሚናው ባሻገር አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአሳታፊነት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው አጀንዳዎችንም በማሰባሰብ በጠቅላላ ጉባኤ በማጽደቅ ለኮሚሽኑ ማስረከቡን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም