በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ብልጽግና ነው - የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ብልጽግና ነው - የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ብልጽግና መሆኑን የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት ተካሂዷል።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ በጣም አጭርና 60 ዓመት ያልሞላው መሆኑን አንስተዋል።
ለውጥ መፍጠር ብቻውን ለውጥን መምራት የሚያስችል ብቃት እስካልተፈጠረ ድረስ የተሟላ የፓርቲ ህልውና እንደማይኖር ተናግረዋል።
ለዚህም ለውጥ መፍጠር ሲባል ስላለ ችግር፣ ድካምና ውድቀት አብዝቶ መናገር ብቻ ሳይሆን መፍትሔም ማፍለቅ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ ብቻ ሳይሆን የምንፈልገውንና የምንወደውን ነገርም አስተሳስሮ ማስቀመጥ፣ ማሳየት ማመላከት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ለሃምሳና ስልሳ ዓመታት የነበረው የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ፣ ልናፈርስና ልንንድ የፈለግነውን ነገር በብዙ ማስረጃ መክሰስ ላይ የተመሰረተ አንጂ ልንገነባ የፈለግነውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት ነበረብን ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩ ኋላ ቀር አሰራር እና ልምምዶችን በማፍረስ በአዲስ እሳቤ የለውጥ ስራዎችን አስቀጥሏል ብለዋል።
ሊያፈርስ የሚፈልገውን ነገርም ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አልቆ መገንባትንም አስቀድሞ የሚያስብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፒያሳን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አልቆ መገንባት የብልጽግና መለያው መሆኑንም አስረድተዋል።
የአንድ ፓርቲ አስኳሉ ሃሳብ በመሆኑ የደረጀ ሃሳብ የሌለው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን በማፍረስ ለውጥ መፍጠር ቢችልም ለውጥ መምራት ካልቻለ ግን የሚያልመውን ለመትከል ይቸገራል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ብልጽግና መሆኑንም ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ፍቱን መድኃኒት የሆነውን የመደመር እሳቤ ቢያመጣም ላለፉት ስድስት ዓመታት አሁንም ከሳሽ እንጂ አማራጭ ሃሳብ ይዞ የመጣ ግለሰብ፣ ቡድንና ፓርቲ አላየንም ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ሀገር በቀል ሃሳብ ቢያቀርቡ ብልጽግና ለመማር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠው ሃሳብ የለሽ ፖለቲከኞች እና ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ ድል፤ የረጅም ጊዜ መከራን የሚያመጡ ይሆናሉ ብለዋል።
በመሆኑም አንድ ፓርቲ ሃሳብ ከነደፈ በኋላም ሃሳቡን በማንሸራሸር የሚያጎለብትበት ጉባኤ እንደሚያስፈልገው አንስተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በዚህ መልክ ለ2ኛ ጊዜ ጉባኤ የሚያዘጋጅበት ዋናው ምክንያትም ያለፈባቸውን ጉዞ በማጠቃለል አዲስ የጉዞ ጅማሮን የሚያስኬድ የተሰናሰለ ሃሳብ የሰነቀ አመራር፣ አሰራርና ደንቦች በጉባኤ መጽደቅ ስላለባቸው መሆኑንም አስገንዝብዋል።
በምክክርና ውይይት የሚፈልቅ ሃሳብም ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ዓመታት የምትጓዝበትን መንገድ የሚቀይስ መሆኑን ገልጸዋል።
ከጉባኤውም በጉባኤው ሂደትም ሆነ ውጤት ዴሞክራሲያዊና አሳታፊነትን እርግጠኝነቱን ለመፈተሽ የሚያስፈልግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ፓርቲዎች ጉባኤ ታሪክም መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባኤ የብልጽግና ጉባኤ ብቻ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው የፓርቲው ጉባኤም "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሃሳብ በቃል የሚነገርና የሚሰነድን በልምምድ ባህል የማድረግ ትኩረት መሰነቁን ገልጸዋል።