በኢትዮጵያ እና በካዛኪስታን መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራል - የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና በካዛኪስታን መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይሰራል - የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እና በካዛኪስታን መካከል ያለውን ፓርላሜንታዊ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዶክተር ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) በካዛኪስታን አምባሳደር እና የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ሳማት ኑር ታታዛ የተመራ የልዑካን ቡድን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው ይህንንም በይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሰብሳቢው አያይዘውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገሮች መካከል መሆኗንም አውስተዋል።
አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ወጣት እንደመሆኑ መጠን የውጭ ሀገር ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ገልፀው ካዛኪስታናውያን ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የካዛኪስታን አምባሳደር እና የፓርላማ አባሉ ሳማት ኑርታዛ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ካዛኪስታን የረዥም ጊዜ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልፀዋል።
ፓርላማ አለም አቀፍ የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው ያሉት ሳማት ኑርታዛ በመጭው መስከረም ወር በካዛኪስታን በሚካሄደው የእስያና አለም አቀፍ የፓርላማ ህብረት ፎረም ላይ ኢትዮጵያ እንድትገኝ ጥሪ አቅርበዋል።
አምባሳደር ሳማት ኑርታዛ አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካዛኪስታን በኩል ወደ ቻይና በየእለቱ በረራ እንዳለው ጠቁመው ካዛኪስታን ምስራቅ እና ምዕራቡን ለማስተሳሰር ምቹ ሀገር በመሆኗ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካዛኪስታን የሰው እና የእቃ መጫን አገልግሎት እንዲጀመር ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበች መሆኗን ገልፀው በሰላም እና ደህንነት በባህል፣ በስፖርት፣ በነፃ የትምህርት እድልም አብሮ ለመስራት ትልቅ እድል መኖሩን ጠቁመዋል።
የበርካታ ሀገራት ዜጎች በካዛኪስታን የነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ናቸው ኢትዮጵያውያንም ከእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በካዛኪስታን በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አምባሳደር ሳማት ኑርታዛ መናገራቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።