ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያቀፈ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያቀፈ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያቀፈ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
ፓርቲው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ አበክሮ እየሰራ ነው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የፓርቲው መደበኛ ጉባዔ በተጨባጭ እመርታዊ ጉዞ ከአያሌ ስኬቶች እና ድሎች ማግስት የሚደረግ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሚዛናዊነትን እና አስተሳሳሪ ትርክትን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበሩትን ተቃርኖዎች የሚያስታርቅ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥን አላማ አድርጎ መቋቋሙን ተናግረዋል።
ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያቀፈ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ መሆኑንም አመልክተዋል።
ፓርቲው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በፍትሃዊነት እና በዘላቂነት ለማረጋገጥ እና ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ብልጽግና ቃልን በተግባር የማረጋገጥ ባህልን መሰረት በማድረግ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ህዝብን ባሳተፈ መልኩ በመሻገርና ፈተናን ወደ እድል በመቀየር ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ነው አቶ አደም የገለጹት።
በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ በመጀመሪያ ጉባዔ ለህዝብ ቃል የተገቡ ጉዳዮችን በመፈተሽ እና የፓርቲውን ቁመና በመገምገም ለቀጣይ ስራዎች የሚሆኑ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ጠቁመዋል።
በመጀመሪያው ጉባዔ ቃል በተገባው መሰረት በስንዴ ራስን ከመቻል ኤክስፖርት ወደ ማድረግ መሸጋገር መቻሉን እና በአረንጓዴ አሻራ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ መገባደጃው መድረሱንም ገልጸዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪስት መዳረሻዎች የማልማት እና ነባሮቹን በማደስ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠር መቻሉንም አብራርተዋል።
ዲጂታላይዜሽንን በማስፋፋት፣ የማዕድን ዘርፍ ኤክስፖርት ገቢን በማሳደግ፣ ከተሞች ለዜጎች ኑሮ የተመቹ የማድረግ እና በአጠቃላይ በርካታ ውጤታማ ሰው ተኮር ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የተገኙ ውጤቶችን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና ተግዳሮቶችን ለመፍታት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።