የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ አስቀርቷል - የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ አስቀርቷል - የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ በአግባቡ መጠቀማቸውን ተከትሎ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚሁ ወቅት የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) የ2017 በጀት አመት እቅድ ከ2016 በጀት አመት እቅድ በላቀ መንገድ መታቀዱን ተናግረዋል።
በተሰራው ስራ ባለፉት ስድስት ወራት ከእቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመዋል።
በሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ የድርጅቱን እና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም ከሁለት ሚልዮን ቶን በላይ ጭነት በባህር መጓጓዙን ገልጸዋል።
በዩኒሞዳል የትራንስፖርት ስርአት ከ654 ሺህ ቶን በላይ ገቢ እቃ እና ከ 174 ሺህ ቶን በላይ ወጪ እቃ ማስተናገድ መቻሉን ጠቁመዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከተሰጡ አገልግሎቶች እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች ከ46 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ኤክስፖርት ላይ የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በኮርፖሬት ስራዎችም ለረጅም ጊዜ ሳይዘጉ የቆዩ ሂሳቦችን መዝጋት ተችሏል ነው ያሉት።
ያልተሰበሰቡ ሂሳቦችን ለመሰብሰብም የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ግዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም አስረድተዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ በአግባቡ በመጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን ጠቁመዋል።
የኮንቴነሮችን የወደብ ቆይታ ለመቀነስ የተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም አብራርተዋል።
በዚህም ካለፉት አመታት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አና በቀጣይም ቀልጣፋ ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።