ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚመጥን አመራር መስጠት ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚመጥን ትጋትና ቁርጠኝነት የተላበሰ አመራር መስጠት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤ እና የሥራ መመሪያ ተቀብለዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ መሾም የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ሃላፊነትና አደራ መጎናጸፍ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የረጅም ዘመን ግንኙነትን የሚያጠናክር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት ሀገር በመሆኗ በኢትዮጵያ ልማትና እድገት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አምባሳደሩ ጠንካራ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በመሆኑም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም አሜሪካ ትልቅ እሳቤን የሚጠይቅ ዲፕሎማሲ የሚከናወንባት መሆኑን ታሳቢ ያደረገ አመራር እንዲሰጡም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ወዳጅን ማብዛት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በቀጣናው ሰላምና ትብብርን ለመፍጠር ጠንካራ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለጀመረችው የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ውጤታማነት ከአሜሪካ ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በቀጣይ በሰላም፣ በጸጥታና በዳያስፖራ ጉዳዮች ዙሪያ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት አምባሳደር ብናልፍ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።


 

አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አማካኝነት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም