በአማራ ክልል ሰላምን የማጽናት ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰላምን የማጽናት ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ
ጎንደር/ ደሴ፤ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የፀጥታ መዋቅሩ ህግ የማስከበር ተግባር ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በሪሁን መንግስቴ ተናገሩ።
በክልሉ ያለፉት ስድስት ወራት የህግ ማስከበር ተግባራትን አፈጻጸም የሚገመግምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በጎንደር እና ደሴ ከተሞች የመክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ቢሮ ሃላፊው በመድረኩ እንዳመለከቱት፤ የክልሉን የፀጥታ መዋቅር መልሶ ከማደራጀት ጀምሮ ለህግ ማስከበር ተልዕኮዎች ብቁ ለማድረግ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል።
በዚህም የጸጥታ መዋቅር አባላት በከፈሉት መስዋዕትነት የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት በመመለስ ልማቱን ማስቀጠል ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት አንድነቱ የጠነከረ የፀጥታ መዋቅር መገንባት ተችሏል ሲሉም አስታውቀዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተገኘውን ሰላም አጽንቶ ለማስቀጠል የፀጥታ መዋቅሩ ዛሬም እንደ ትናንቱ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት ይወጣል ብለዋል።
እንደ ምክትል የቢሮ ሃላፊው ገለጻ፤ በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ የህግ ማስከበር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በመድረኩ በጥንካሬ የሚነሱትን በተሞክሮ በመውሰድና ጉድለቶችን በማረም ህዝቡ በአሁኑ ወቅት ያገኘው ሰላም እንዲጸና የፀጥታ መዋቅሩ ለላቀ ተልዕኮ እራሱን እንዲያዘጋጅ ይደረጋል" ሲሉም ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው እንዳሉት፥ በፀጥታ መዋቅሩ ቅንጅታዊ ተግባር በአሁኑ ወቅት የከተማውን ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል።
በከተማው የሰፈነው ሰላም የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ፣ አዳዲስ የልማትና የኢንቨስመንት ፕሮጀክቶችም ወደከተማው እንዲመጡ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዘለቀ አለባቸው እንደገለጹት፥ በዞኑ ሰላምን በዘላቂነት በማጽናት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው።
በዚህም የአጥፊዎችን ሴራ በማክሸፈ በዞኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በአግባቡ መከናወን እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ነው የተናገሩት።
ህብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆና ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላም መጠበቁ ለተገኘው ውጤት አስተዋጾ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ በርካታ ታጣቂዎች የተህድሶ ስልጠና እየወሰዱ ወደህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ከማድረግ ባለፈ ወደ ፀጥታ መዋቅሩ በመግባት በሰላም ማስክበር ህዝቡን እየካሱ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው፤ በተቀናጀ መንገድ በተከናወነ የህግ ማስክበር ሥራ የክልሉ ሰላም ለማጽናት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆንና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ ተግባራት አሁንም በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ ተደራጅቶ ለሰላሙ መከባር ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን ሆኖ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡