ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና እምቅ ሀብቶች ሀገራዊ እሴቶችን ለማዳበር አቅም የሚፈጥሩ ናቸው - ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና እምቅ ሀብቶች ሀገራዊ እሴቶችን የማዳበር አቅምና እድል እንዳላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ከአራት ዓመት በፊት በ81ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል መገኘታቸውንና በበዓሉ ስርዓት መደመማቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።


 

በዓሉ የተዘጋጁ የተለያዩ እና ያልተለመዱ ምግቦች፣ ሙዚቃው፣ አልባሳቱ፣ ከፈረስ ትርዒቱ ጋር ተደምሮ ድንቅ ድባብ እንደነበረው አውስተዋል።

በወቅቱ ሴት ፈረሰኞች የዚህ አካል ሆነው መመልከታቸው ከፍተኛ አድናቆት እንደሰማቸውም አመልክተዋል።

እንደ ሀገር ያሉ ብዙ ታሪካዊ እና በስፋት የማይታወቁ ኹነቶች ሲመነዘሩ ለአካባቢው ሰው ብዙ ዕድሎችን ከማመቻቸት ባለፈ ያሉንን ዕሴቶች እያዳበርን ማሳደግ የምንችልበትን ዐቅም ይፈጥራሉ ብለዋል ኃላፊዋ በመልዕክታቸው።


 

ዛሬ በሚከበረው 86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል ብዙ የሀገር ውስጥም የውጭ ሀገር ጎብኚም ይህን ድንቅ ትዕይንት ይታደማሉ ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

አካባቢውም ነቅቶ ሰላሙን በመጠበቅ ይህን በዓል ከዓመት ዓመት ማከናወን መቻሉ የወደፊት ዕድሉን የሚያጠናክር እና ለፌስቲቫል ቱሪዝም ገቢ ተቋዳሽ ለመሆን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም