ቀጥታ፡

የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማሻሻያዎች የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ድርሻ እንዲያድግ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማሻሻያዎች እና የተለያዩ ማበረታቻዎች የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ማስቻሉ ተገለጸ፡።

ከዚህ ቀደም የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራችና አቅራቢዎች በነበሩባቸው በርካታ ተግዳሮቶች በሙሉ አቅማቸው መስራት አለመቻላቸውን በተደጋጋሚ ሲያነሱ ይደመጡ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በመድኃኒት ምርትና አቅርቦት የአገር ውስጥ ፍጆታን በሚገባው ልክ መሸፈን አለመቻሉ ይታወቃል።

ለውጡን ተከትሎ መንግስት በነደፋቸው አዳዲስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመደገፍ እንዲሁም በተመቻቹ ማበረታቻዎች በመታገዝ የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢዎች አቅም አድጓል።

የተወሰዱት እርምጃዎች መድኃኒት አምራችና አቅራቢዎች በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒትና ህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አምራች ዘርፍ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ፥ መንግስት የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢዎችን ድርሻ ለማሻሻል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከለውጡ በኋላ የተደረጉ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማሻሻያዎች እንዲሁም የሚሰጡ ማበረታቻዎች የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ድርሻ እንዲያድግ አስችለዋል፡፡

በዚህም ስምንት በመቶ የነበረው የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ድርሻ ወደ ሰላሳ ስድስት በመቶ እንዲያድግ መደረጉን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

በቀጣይም የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች በጤናው ዘርፍ ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ አስተዋጾአቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የአፍሪኪዩር ኢትዮጵያ የመድኃኒት ፋብሪካ ባለቤት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ መንግስት በበኩላቸው፥ የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾችን ለማበረታታት የወጡ ፖሊሲዎችና የስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ዘርፉን ውጤታማ እያደረጉት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከፖሊሲና ስትራቴጂ በተጨማሪ መንግስት የተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዘርፉ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመፍታት ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማስቻል የሚቀርበው የስራ ማስኬጃ የፋይናንስ አቅርቦት በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም