ቀጥታ፡

በጌዴኦ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ዲላ፤ጥር/23/2017 (ኢዜአ)፦በጌዴኦ ዞን ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በንቅናቄ በተሰራ ሥራ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ የሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ ህብረተሰቡ በቦንድ ግዥ በነቂስ በመሳተፍ ዳግም አሻራውን እያኖረ መሆኑም ተመላክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሮቤ ለኢዜአ እንደገለጹት፥የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ወደዞኑ መምጣትን ተከትሎ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ ተከናውኗል።

በዚህም የ16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ የተፈጸመ ሲሆን ተጨማሪ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይም ቃል መገባቱን ገልጸዋል።

በድጋፉ ከመንግስት ሠራተኛውና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ ተቋማትና ማህበራትም መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

የዞኑ ህዝብ በቦንድ ግዥ በነቂስ በመሳተፍ ዳግም አሻራውን ማኖሩንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ በዞኑ የነበረውን የአንድ ወር ቆይታ አጠናቆ ለወላይታ ዞን መሰጠቱን ያነሱት አቶ ብርሃኑ፣ በበጀት ዓመቱ ቀጣይ ወራት ለግድቡ የሚሰበሰበውን ገቢ 60 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም