ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች- አምባሳደር ለገሠ ገረመው

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ያላትን ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለገሠ ገረመው ገለጹ።

አምባሳደር ለገሠ ገረመው ኃይሌ ትናንት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ አቅርበዋል፡፡

አምባሳደሩ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሁለቱ አገራት መካከል ለረጅም ጊዜ ፀንቶ የቆየውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተለይ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በባህል እና በአቪዬሽን ዘርፎች ትኩረት በማድረግ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል አምባሳደር ለገሠ የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የህዝብ ለህዝብ ቅርርብና ትስስር በመፍጠር ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑንና ለአየር መንገዱ ሥራ መሳካት በናይጀሪያ መንግስት እየተደረገ ላለው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ አገራቸው በአፍሪካ ጉዳዮች እና በሌሎችም የጋራ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበትና በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በቆይታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር በሁሉም ዘርፎች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመንግስታቸው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለአምባሳደሩ መልካም የስራ ጊዜ እንዲሆንላቸው መመኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም