ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለ85ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክበረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለ85ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክበረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(አዜአ)፦ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ለ85ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክበረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
እንኳን 85ኛው ለአገው ፈረሰኞች ቀን አደረሳችሁ!
እንኳን ታምፁናስ!
ከዛሬ 85 ዓመት በፊት ለተመሰረተውና በህዝባዊ መሰረቱ ፀንቶ ለቆየው ለአገው ፈረሰኞች በዓል እንኳን አደረሳችሁ። የአገው ሕዝብ የሀገሩን ክብር፣ አንድነት እና ማህበረሰባዊ ማንነቱን በሁለተናዊ ጀግንነቱ አፅንቶ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡
ይህ ቀደምት እና ሥልጡን ሕዝብ ታሪኩን፤ባህሉን እና እሴቱን ጠብቆ ያቆየበት ትጋትና በሌሎች ኢትዮጵያውያንም ዘንድ እንዲከበሩ ለማድረግ ያሳየው ሥልጡን አካሄድ የህዝቡን ጥንታዊነት፤የቱባ ባህሎች ባለቤትነት ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ፈር ቀዳጅ ሕዝብ መሆኑን በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል፡፡
የዚህ ኩሩ ሕዝብ ፍሬ የሆነው የአገው ፈረሰኞች ማኅበርም ቀደምት አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ልዑዋላዊነትና አንድነት በጀግንነት የከፈሉትን ሰማዕትነት በክብር እየዘከረ ከሦስት ትውልድ በላይ ተሻግሯል፡፡ይህም የአገው ሕዝብ ሀገሩን እና ለሀገሩ ክብር ዋጋ የከፈሉትን ሁሉ አክብሮ የሚያስከብር አመስጋኝ ሕዝብ መሆኑን ያሳያል፡፡
ዘንድሮም የሀገር ባለውለታ የሆኑ ጀግና ፈረሰኞች ከነ ስልጡን ፈረሶቻቸው በሚዘከሩበት የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል ከምንጊዜውም በላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብለው ይታዩበታል፡፡
የአገው ፈረሰኞች እና ሌሎች ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር ተባብረው ነጻነታችንን ማስከበር እንደቻሉት ሁሉ ፤ እኛም የዚህ ዘመን ትዉልድ አባላት ትናንት እነዚያ አባቶቻችን የነበራቸዉን የሰንደቅዓላማ ክብር እና ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕትነት በማስታወስ ወቅቱ የሚጠይቀዉን የብሔራዊ አርበኝነት ግዳጅ ልንወጣ ይገባል፡፡
በዓሉ በዓመታት ሂደት ዉስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ላደረጉ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብም የተጀመሩት ተግባራቶች እንዲሳኩ የክልሉ መንግስት አስፈላጊዉን ሁሉ እያደረገ እና በቀጣይም የሚያደርግ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ ፡፡ አመሰግናለሁ!!
መልካም በዓል!
