ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ከአባል አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነቷን ባስከበረ መልኩ ጠንካራ ተሳትፎ ታደርጋለች- አምባሳደር ለምለም ፍስሃ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ከአባል አገራት ጋር በተለያዩ መስኮች የጋራ ተጠቃሚነቷን ባስጠበቀ መንገድ ጠንካራ ተሳትፎ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ለምለም ፍስሃ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የቴክኒክ ኮሚቴ ትናንት ስብሰባውን አካሂዷል።

ውይይቱን የመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አምባሳደር ሚኒልክ ዓለሙ ናቸው።

መድረኩ በብራዚል የብሪክስ ፕሬዝዳንትነት ዓመት በሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ለምለም ፍስሀ በተጠናቀቀው 2024 የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስኬቶች እና በ2025 ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ስለሚኖራት እንቅስቃሴ በተመለከተ አጠቃላይ ገለጻ አቅርበዋል።

አምባሳደር ለምለም ብሪክስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ዓላማ ገቢር ለማድረግ ተጨማሪ ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ማዕቀፍ አባል አገራት ጋር በግብርና ፣ በመሠረተ ልማት፣ በጤና ፣ በትምህርት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያስጠብቅ መንገድ ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚኖራት ገልጸዋል።

ከ21 የመንግሥት ተቋማት የተወከሉ ተወካዮች ኢትዮጵያ በ2025 በብራዚል የብሪክስ ፕሬዝዳንትነት ወቅት እንደ አገር ለማሳካት ለታቀደው ግብ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የቴክኒክ ኮሚቴው በተለያዩ ዘርፎች መካከል ያለውን ግንኙነትም የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ መወያየቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም