የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ በላሊበላ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ ተግባራዊ የተደረገው የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለፀ።
በላሊበላ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ዙሪያ ያተኮረ ውይይት በዛሬው ዕለት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በላሊበላ ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ፣ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፣ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮማቴ ምክትል ሰብሳቢ፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በላሊበላ ቅርስ ጥገና ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት እየተሰሩ ያሉ የመሸጋገሪያ ድልዶይ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የመፋሰሻ ቦይ ከፈታ፣ የቅርሶች ጥገና፣ የላንድ ስኬፕ ስራዎች መልካም እንደሆኑ ተመላክቷል።
በዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች የሚበረታቱና በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ በመሆናቸው ቀጣይነት እንዲኖራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
የላንድ ስኬፕ ስራዎቹ በሁሉም የቅርሱ አካባቢዎች እንዲሰፉ ተጠይቋል።
የቅርስ ጥገና ስራው በጥራት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አማካሪዎች በቦታው ተገኝተው የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው ተገልጿል።
የከተማዋ ነዋሪዎች የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሸልተር የማንሳትና የመቀየር ስራው በቶሎ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክትና የሸልተሩ ፕሮጀክት ራሳቸውን የቻሉ መሆናቸውንና ሸልተሩን የመቀየር ስራውን ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ በበኩላቸው የዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ስራውን እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።
የቅርስ ጥገና ስራዎችን ለህዝብ በማስተዋወቅ በኩል በፕሮጀክቱ የነበረውን ክፍተት ወደ ፊት በማሻሻል መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሸልተሩ ጉዳይ በማያዳግምና በቅርሱ ላይ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ለመስራት ትኩረት መሰጠቱንም አስገንዝበዋል።