አገልግሎቱ የቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ትግበራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ የቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ትግበራ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ ደንበኞች የፍጆታ ክፍያና የኢነርጂ ሽያጭ ስርዓቱን ይበልጥ ቀላል እና ምቹ ለማድረግ ቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ትግበራ መጀመሩን ገለፀ።
አገልግሎቱ 'ዩኒፋይድ ፕሪፔይመንት' በተሰኘው ፕሮጀክት የስማርት ነጠላ ፈዝ ቆጣሪዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አሳውቋል።
ለፕሮጀክቱ ትግበራ አስፈላጊ ዕቅዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ከ2 ሺህ 55 አዲስ ስማርት ነጣላ ፌዝ ቆጣሪዎች የመግጠም ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።
ቆጣሪዎቹ ደንበኞች ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ካሉበት ቦታ ሆነው ቶከን በቴሌ ብር በመግዛት ኢነርጂ እንዲሞሉ እንደሚያስችል አመልክቷል።
እስካሁን በአዲስ አበባ የባልደራስ ኮንዶሚኒየም፣ ፈረስ ቤት እና የካ ሳይት 100 ቆጣሪዎች፣ ባቱ እና መካኒሳ ኮንዶሚኒየም 1 ሺህ 432 ቆጣሪዎች እንዲሁም ሲ ኤም ሲ ልዩ ቤቶች ጀርባ የመከላከያ ቤቶች 523 ቆጣሪዎች እንደተገጠሙ ጠቅሷል፡፡
የፕሮጀክቱ ትግበራ ደንበኞች ከፍጆታ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያሉ ቅሬታዎች በመቅረፍ እና የደንበኞች እንግልት በማስቀረት ባሉበት ቦታ ሆነው ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ኢነርጂ መግዛት የሚያስችላቸውን ስርዓት ለመፍጠር እንደሚያስችል መግለጫው ጠቁሟል።
በፕሮጀክቱ ግማሽ ሚሊዮን የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን በዘመናዊ ቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች እንደሚቀየሩ ገልጿል።
ከነዚህም መካከል 125 ሺህ በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ ለሶስት ፌዝ ቆጣሪ ተጠቃሚ ደንበኞች ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ 25 ሺህ ነጠላ ፌዝ ስማርት ቆጣሪዎች ደግሞ አዲስ አበባ ለሚገኙ ደንበኞች እየተቀየረ መሆኑን ገልጿል።