ለሰብዓዊ መብቶች የሚደረግ ጥበቃና ክትትል ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ይሰራል- ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰብዓዊ መብቶች የሚደረግ ጥበቃና ክትትል ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ይሰራል- ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች የሚደረግ ጥበቃና ክትትልን በማጠናከር ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው የአቶ ብርሃኑ አዴሎን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዕጩ ዋና ኮሚሽነርነት ሹመት አጽድቋል።
አዲሱ ዋና ኮሚሽነር ለኢዜአ እንዳሉት በኃላፊነት ዘመናቸው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች የሚደረገው ጥበቃና ክትትል በማጎልበት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የተጠናከረ የሰብዓዊ መብት ክትትልና ጥበቃ በማድረግ የሰዎችን መብት ለማስከበር የተቀናጀና የተጠናከረ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፣ እያንዳንዱን ባለድርሻ አካል ያሳተፈ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ክትትል አቅምን ማሳደግም ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለልተኝነትና ተዓማኒነቱን ጠብቆ ዜጎችን ለማገልገል ከመቼውም ጊዜ በላይ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና አያያዝ ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ከኮሚሽኑ በተጨማሪ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያማከለ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ክትትል አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሲሆን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች በሕንድ ሀገር የሰሩ መሆኑ ታውቋል።