ባህር ዳር ከተማ ያላትን የቱሪዝም ፀጋዎች መጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው

ባህር ዳር ጥር 22/2017 (ኢዜአ)፦ ባህር ዳር ከተማ ያላትን የቱሪዝም ፀጋዎች መጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ ''ጥርን በባህር ዳር'' ሁነቶች የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም ተገልጿል።


የ"ጥርን በባህር ዳር " ሁነቶች አካል የሆነው ጥርን በባህር ዳር የባህል ዐውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ጊዜው ታከለ እንዳሉት፤ በከተማው ያለውን የቱሪስት መስህብ ፀጋ አጉልቶ የመጠቀም ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በተለይም ''ጥርን በባህር ዳር'' እየተከናወኑ ያሉ ሁነቶች የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት በማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሆነም ተናግረዋል።

የጀልባና ታንኳ የጣና ሃይቅ ላይ ሽርሽር፣ ዐውደ ርእዮች፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትና የመሳሰሉት የጥርን በባህር ዳር ሁነቶች ማክበር ከተመዋን የቱሪዝም መዳረሻነት በመጨመር አስተዋጽኦዋቸው እንዲጎላ ያደርጋል ብለዋል።

ባህር ዳር ከተማ በተፈጥሮ ያላትን ሃብት አጉልቶ በማውጣትና በማስተዋወቅ ዋና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የከተማዋን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን የበለጠ በማጉላት የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን የሚያሳደጉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ናቸው።

በባህር ዳርና አካባቢው የቀደሙ የባህል መገለጫ ፀጋዎች እንዳይረሱና የአካባቢው ማህበረሰብ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑም ገልፀዋል።

በተለይም የአልባሳት፣ የመጠጫና የምግብ መያዣ ቁሳቁሶች፣ ከከብት ቆዳ የሚሰሩ ምንጣፎችና ሌሎች ቁሶች የህብረተሰቡን የኑሮ ዘዴና ፍልስፍና አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ዐውደ ርዕዩ የባህል ፀጋዎችን በአደባባይ አጉልቶ በማሳየት ለትውልዱ የበለጠ ለማጉላት ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከተማዋን ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ሲሆን ጎብኝዎችና ኢንቨስተሮች ራሳቸውንና ከተማዋን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

ወጣት ህይወት ደጀን በበኩሏ፥በዐውደ ርዕዩ የባህል አልባሳትን ይዛ መቅረቧን ጠቅሳ፤ ይህም ከሰዎች ጋር ትውውቅ ለመፍጠርና አልባሳቱን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ገልጻለች።

የአዋቂዎችንና የህጻናት አልባሳት የመስራትና የመጥለፍ ስራ እንደምታከናውን የገለጸችው ወጣቷ፤ ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ጊዜና ቦታ ወስኖ እየሰራ ላለው ተግባር አመስግናለች።

ከጥር 22 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው የጥርን በባህር ዳር የባህል ዐውደ ርዕይ የተለያዩ የባህል አልባሳትና ቁሶች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም