ቀጥታ፡

የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ሀዋሳ፤ ጥር 22/2017 (ኢዜአ)፡-በመድኃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሀገር ውስጥ የመድሀኒት ምርት ድርሻን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቅናው ካውዛ የመድኃኒት አቅርቦትን በዘላቂነት ለማሻሻል ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥ ተመርተው የሚቀርቡ መድኃኒቶችን መጠን ለማሳደግ ግብ ተቀምጦ በተሰራ ሥራም ከአጠቃላይ የመድሀኒት አቅርቦት የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአሥር ዓመት ውስጥ በሀገር ውስጥ የተመረቱና በጣም አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች መጠን ከ50 በመቶ በላይ ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እንደ አቶ አቅናው ገለጻ የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ለጥሬ ዕቃ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይገጥማቸው ከጤና ሚኒስቴርና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው።  

ከሁለት ዓመት በፊት ከአጠቃላይ የመድሀኒት አቅርቦት የሀገር ውስጥ ድርሻ ስምንት በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ይህን ለመቀየር በተሰራው ሥራ በአሁን ወቅት ከ30 በመቶ በላይ ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።

ለዚህም እስከ 8 ቢሊዮን ብር የሚሆን የግዢ ውል ከሀገር ውስጥ የመድሀኒት አቅራቢዎች ጋር መገባቱን  ነው አቶ አቅናው የጠቆሙት።

እንደ አቶ አቅናው ገለጻ ቀደም ሲል አገልግሎቱ የሚያቀርባቸውን መድኃኒቶች፣ የሕክምና መሳሪያዎችና ሌሎች ግብአቶችን የመቆጣጠርና የማስተዳደር ሥራዎች ክፍተት ነበረበት።

ይህን በማስተካከል ለህብረተሰቡ መድኃኒቶችና ሌሎች ግብአቶችን በአግባቡ ለማድረስ የዲጂታል የአሰራር የሥርአት ዘርግተናል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር አስተባባሪና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ በበኩላቸው፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭትን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ በተቋሙ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅርንጫፉ ስር ያሉ የመንግስት ጤና ተቋማት በተለይም ለወባ እና ቲቢ ህክምና እንዲሁም ለቤተሰብ ምጣኔና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ መድኃኒቶችና ክትባቶችን በቀጥታ ከተቋሙ ማግኘት የሚያስችላቸው ፕሮጀክት ተቀርፆ ሥራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

ይህም ከዚህ በፊት በዞኖችና ወረዳዎች ላይ የነበረን መዘግየት በማስቀረት በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የመድኃኒት እጥረትና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት ማስቻሉን አስረድተዋል።

ዲጂታል የአስራር ሥርአቱ ጤና ተቋማት ለመድሀኒት ማጓጓዣ ያወጡት የነበረን ወጪ በማስቀረት በኩል ጉልህ አስተዋጾ ማድረጉንም አቶ ዘመን አክለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም