በክልሉ ለቡና ልማት ትኩረት ባልተሰጠባቸው አካባቢዎች ልማቱን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለቡና ልማት ትኩረት ባልተሰጠባቸው አካባቢዎች ልማቱን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው

ቦንጋ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡና ልማት ትኩረት ባልተሰጠባቸው አካባቢዎች ልማቱን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጁአብ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክልሉ በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ከፍተኛ የመልማት አቅም አለው።
ልማቱን ለማስፋፋት ነባሩን ቡና ከመጎንደል ባለፈ በአዲስ መሬት ቡና ለመትከል ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፣ ለዘንድሮ ተከላ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ከ71 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
ክልሉ ለቡና ልማት ያለውን አቅም ለመጠቀም የማሳ ሽፋን የማስፋትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
"ለዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በ63 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡና በማልማት አጠቃላይ ሽፋኑን ከ582 ሺህ ሄክታር በላይ ለማድረስ ተችሏል" ብለዋል።
ዘንድሮ ለአዲስ ተከላ የተዘጋጀ ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ጨምሮ ለቡና ልማት ትኩረት ባልሰጡ አካባቢዎችም ልማቱን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀጣይም በዳውሮ፣ ኮንታና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች 480 ሺህ ሄክታር ማሳ ለማልማት መሬቱን የመለየት ሥራ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
የማሳ ሽፋንን ከማስፋት ባለፈ ምርታማነትን ለማሳደግ የእንክብካቤ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ ያረጁ የቡና ተክሎችን የመጎንደልና ነቅሎ በአዲስ የመተካት እንዲሁም ሌሎች መሰል ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
"ለአብነትም በተያዘው ዓመት በ4ሺህ 820 ሄክታር መሬት ላይ ያለ ያረጀ ቡናን የመጎንደልና ነቅሎ በአዲስ የመተካት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
በክልሉ በቡና ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ የቡና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በእርጅና ምክንያት ምርታማነታቸው የቀነሰውን የቡና ተክል የመጎንደልና አዲስ ለመትከል እየተዘጋጁ መሆኑን ገልፀዋል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ታምሩ ታደሰ፣ ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በቡና ልማት ሥራ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በ2 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ ላይ ቡና እያለሙ መሆኑን ገልጸው፣ ዘንድሮ በ1 ሄክታር ተጨማሪ ማሳ ላይ ቡና ለመትከል የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ዝርያ ችግኝ በማህበር ማዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።
አምስት ሄክታር የቡና ማሳ እንዳላቸው የገለጹት ሌላኛው አርሶ አደር አባተ አዶ በበኩላቸው፣ ዘንድሮ በአንድ ሄክታር ተጨማሪ መሬት ላይ ቡና ለማልማት የማሳና የዘር ዝግጅት አድርገዋል።
በልማቱ ውጤታማ ለመሆንም በግብርና ባለሙያዎች ምክር መሰረት አስፈላጊውን ማዳበሪያ ከመጠቀም ባለፈ የአረም ቁጥጥርና እንክብካቤ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።