የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች በቀጣይነት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው- የባንኩ ኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች በቀጣይነት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው- የባንኩ ኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር
አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- የዓለም ባንክ በትግበራ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርሞች ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን የባንኩ ኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ እና ከዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋካ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ሁለን አቀፍ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ አድንቀዋል።
ባንኩ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ዘርፎች ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የኢንቨስትመንት መጠን እንዳለው አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ለዓለም ባንክ የስራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አስመልክቶ ያሉ ወቅታዊ መረጃዎችን አጋርተዋል።
መንግስት በሪፎርሙ አማካኝነት በታክስ እና የፋይናንስ ዘርፉ ማሻሻያ በማድረግ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ይህን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ለጋሽ አካላት በዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር የፋይናንስ ማዕቀፍ በኩል እያደረጉት ላለው ድጋፍም ሚኒስትሩ አመስግነዋል።
ዓለም ባንክ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን በ2030 በአፍሪካ 300 ሚሊዮን ዜጎችን የኤሌክትሪክ ብርሀን ተጠቃሚ ለሚያድረገው 'ሚሽን300' ፕሮጀክት ትግበራም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
ታዳሽ ኃይል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ ቁልፍ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው፤ ሀገሪቷ በታዳሽ ኃይል ዕምቅ አቅም እንዳላት አውስተዋል።
በመሆኑም ታዳሽ ኃይል ዘርፍ ኢትዮጰያ ከዓለም ባንክ ጋር በአጋርነት ለመስራት ሁነኛ የትብብር መስክ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ ኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ እየተገበረችው የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ በማድነቅ በሪፎርሙ የተገኙ ውጤቶችን አድንቀዋል።
የዓለም ባንክ ሪፎርሞች ስኬታማ እንዲሆኑ አሁንም ድጋፉን በቀጣይነት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ የሪፎርሙን ጥልቀት በመጨመር ለግሉ ዘርፍ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ኢትዮጵያ እና ዓለም ባንክ ያላቸውን ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።