በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው በኮሚሽኑ የሶስት አመት ስትራቴጅክ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ገምግሟል።
የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሚሽኑን የአፈጻፀም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።
ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተመርጠው የሚመጡበት ሁኔታ ጥሩ የዴሞክራሲ ልምምድ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ቀሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገራዊ ምክክሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በቀጣይ ወደ ውይይቱ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሂደቱ አካታችና አሳታፊ የነበረና ጥሩ ተሞክሮ የተወሰደበት ነው ያሉት ሰብሳቢው ይህም በራስ አቅም ችግሮችን የመፍታት እና የውይይት ባህልን እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።
በሪፖርቱ ከቀርቡት ጉዳዮች መካከል የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን እንዲሁም ሌሎች መሠል የማህበረሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ በሃገራዊ ምክክር ሂደቱ ከፍ ማለት እንዳለበት ተመላክቷል።
ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲቋጭ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያሳድጉ ጥሪ መቅረቡንም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።