አፍሪፖልን ማጠናከር የአፍሪካ የፖሊስ ተቋማት በዓለም መድረክ ላይ ያላቸውን ሚና ያሳድጋል- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪፖልን ማጠናከር የአፍሪካ የፖሊስ ተቋማት በዓለም መድረክ ላይ ያላቸውን ሚና ያሳድጋል- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- አፍሪፖልን ማጠናከር የአፍሪካ የፖሊስ ተቋማት በዓለም መድረክ ላይ ያላቸውን ሚና እንደሚያሳድግ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
26ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት(EAPCCO) ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በሩዋንዳ ኪጋሊ መካሄዱን ቀጥሏል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በጉባዔው ላይ እየተሳተፋ ይገኛሉ።
ኮሚሽነር ጀነራሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአፍሪካ ህብረት የቴክኒክ ተቋም የሆነው አፍሪፖልን (AFRIPOL) በአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት የፖሊስ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር የማጠናከር ተልዕኮ ወስዶ እየሰራ ነው።
ስለሆነም ሁሉም የቀጣናው አባል ሀገራት ተቋሙን ለማጠናከር በትብብር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የኮሚሽነር ጀነራሉ ሀሳብ በድርጅቱ አባል ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።