ቀጥታ፡

የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና አዛን ውድድር መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፦ የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና አዛን ውድድር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

የ2017 የኢትዮጵያ ዓለም የቁርአንና አዛን የውድድር የሽልማት ስነ ስርአትም የፊታችን እሁድ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ዳኞች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርአንና የአዛን ውድድር የላቀ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተው ለዚህም አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።


 

የዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና የአዛን ውድድር ዋና ኃላፊ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ60 አገራት ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የቁርአንና የአዛን ውድድር የሽልማት ስነ ስርአትም ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው ከውድድርም ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት ለውድድሩ መሳካት ላደረጉት እገዛም አመስግነዋል።


 

ዓለም አቀፉ የቁርአንና አዛን ውድድር በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና በዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር የተዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ እያደገ በመምጣቱ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።

በቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በተሰሩ በርካታ ስራዎችም ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎች እና ውድድሮች የሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ።

መሰል ዓለም አቀፍ የውድድር መርሃ ግብሮችንና ጉባኤዎችን በማስተናገድ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ማሳደግ የሚያስችል ትልቅ አቅምም ገንብታለች።

ለዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከማልማት ባለፈ ነባሮችን የማደስ ስራዎች ተሰርተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ምርጫቸው ያደረጉ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ በማድረጉ ከአምስት ዓመታት ወዲህ የጎብኚዎች ቁጥር በ40 በመቶ ማደጉንና በአፍሪካ የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረባቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም