ቀጥታ፡

ማህበሩ ከ59 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን በልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ

ደሴ ጥር 21/2017 (ኢዜአ) -የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞኖች ባከናወናቸው የልማት ተግባራት ከ59 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ።

ማህበሩ በ"መሰላል" ፕሮጀክት በደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞኖች የተሰሩ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ አካሂዷል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የመሰላል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዘራ ታደሰ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በተለያዩ ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት በሁለቱ ዞኖች በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቀጥታ ድጋፍ፣ በመልሶ ማቋቋምና በሌሎችም ዘርፎች ከ59 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም ለተፈናቃዮች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአረጋዊያን የምግብና የአልባሳት ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ነው የገለጹት።

ለዚህም ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን አስታውሰው፣ "በድጋፉ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ማነቃቃት" ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በስኬት ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በመደረግ ላይ መሆኑን ነው አቶ ዘራ ያስታወቁት።


 

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመሰላል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋሁን ዘውዴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ከኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በዞኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ናቸው።

በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት በ52 ሚሊዮን ብር ወጪ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቀጥታ ድጋፍ፣ በኑሮ ማሻሻያና በሌሎችም የልማት መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ዘውዱ በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትንና ሽፋኑን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

'"በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በተገነቡ ሰባት የመጠጥ ውሃ ተቋማት ከ23 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል" ሲሉም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተገነባላቸው የውሃ ተቋም የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው መቃለሉን የገለፁት ደግሞ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የቀበሌ 031 ነዋሪ ወይዘሮ ሉባባ ይመር ናቸው።

ቀደም ሲል ከአንድ ሰዓት በላይ በእግር በመጓዝ ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃ ይጠቀሙ እንደነበረ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ለእንስሶቻቸው ጭምር ውሃ እንደልብ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ከማህበሩ ተወካዮች በተጨማሪ የደቡብ ወሎና የሰሜን ወሎ ዞን አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም