ቀጥታ፡

ተንቀሳቃሽ የስራ ባህሪ ታሳቢ አድርጎ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት  ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል 

ጋምቤላ ጥር 21/2017 (ኢዜአ) ተንቀሳቃሽ የስራ ባህሪ ታሳቢ አድርጎ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት  ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኤክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ተናገሩ ። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች መስሪያ ቤቱ በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ሰራተኞቹ በኤች አይ ቪ/ኤድስና ሌሎች በሽታዎች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል። 

ከመድረኩ ተሳታፊ ሰራተኞች መካከል ወይዘሪት እጅጋየሁ አረጋ በሰጡት አስተያየት መስሪያ ቤቱ በየጊዜው የሚያመቻቸው የኤች አይ ቪ/ኤድስ እና ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የምክርና የደም ምርምራ አገልግሎት ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ እየሆናቸው ነው። 

መስሪያ ቤቱ የሰራተኛውን ተንቀሳቃሽ የስራ ባህሪ ታሳቢ በማድረግ እየሰጠ ያለው የኤች አይ ቪ/ኤድስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች በየስራ ቦታቸው ጤናቸውን እንዲጠብቁ እንዳስቻላቸው የገለፁት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ተመስገን ሶዶኖ ናቸው። 

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ዘይኔባ ዓሊም  ኤች አይ ቪ/ኤድስን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሰራተኛው መከላከል እንዲችል መስሪያ ቤቱ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየሰጣቸው  መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም በየጊዜው እየተሰጣቸው ያለው የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክርና የደም ምርመራ፣ የስኳር፣ የግፊትና የሌሎች የጤና ምርመራዎች ሰራተኛው እራሱን  አውቆ ጤናውን እንዲጠብቅና እንዲከታተል በማድረግ ረገድ ትልቅ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል። 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ በዳሶ መድረኩ ላይ እንዳሉት ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ከጤና እክልነቱ ባለፈ አምራቹን ዜጋ በመጉዳት ልማትን የሚያደናቅፍ በሽታ ነው። 

መስሪያ ቤቱ በየጊዜው ለሰራተኞቹ ከጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀት በኤች አይ ቪ/ኤድስ ሌሎች በሽታዎች ዙሪያ አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የምክርና የደም ምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ እራሳቸውን ከተለያዩ በሽታዎች እንዲጠብቁ እያደረገ ነው ብለዋል። 

ባለፉት ሶስት ወራትም የዓለም የኤች አይ ቪ/ኤድስን ቀን በማስመልከት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ለሚገኙ ሰራተኞቹ በኤች አይ ቪ/ኤድስና ሌሎች ተላለፊና ተላለፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክርና ደም የምርምራ አገልግሎት እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። 

በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ሰራተኞቹም ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የምክርና የደም ምርመራ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉንም አቶ አህመድ አስታውቀዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም