በገንዳ ውኃ ከተማ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታን ለማስቀረት ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በገንዳ ውኃ ከተማ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታን ለማስቀረት ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው
መተማ፤ጥር 21/2017 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ህገ ወጥ የከተማ መሬት ወረራንና ግንባታን ለማስቀረት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተካልኝ ማዘንጊያ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በከተማዋ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ተበራክቶ ቆይቷል።
ህገ ወጥ ተግባሩን በመከላከል ለማስቀረት ከተቋቋመ ግብረ ኃይል ጋር በመቀናጀት በተከናወነው ሥራም 300 ህገ ወጥ ግንባታዎችና የመሬት ወረራዎችን በመለየት ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።
እስካሁንም በህገ ወጦች ተይዞ የነበረ ከ24 ሄክታር በላይ የከተማ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በከተማው ፕላን መሰረት የንግድ ቦታዎች ባለ አራት ፎቅ መገንባት የሚያስገድድ ቢሆንም አንዳንድ ባለሀብቶች የተረከቡትን ቦታ በወጣለት ደረጃው መሰረት መገንባት ሲገባቸው ኮንቴይነር በማስቀመጥ በኪራይ ይጠቀሙ የነበረን አሰራር ለመቀየር እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
በተወሰደው እርምጃም የህብረተሰቡ ድጋፍ የጎላ መሆኑን አንስተው፤ እገዛውም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መላኩ አለበል በሰጡት አስተያየት፤ በከተማዋ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
"ባለሃብቱ የቆርቆሮ ኮንቴይነር በማስቀመጥ በኪራይ መጠቀምን እንጂ የከተማ እድገትና ውበት አያሳስበውም ነበር" ያሉት ነዋሪው፤ አሁን ግን በርካታ ባለሃብቶች ወደ ህንፃ መገንባት መሸጋገራቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
ህገ ወጥ ኮንቴይነሮች ፈርሰው ሕንፃ እንዲጀመር መደረጉ ለከተማዋ ውበትና የስራ እድል መፈጠር አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማድረጉን የገለጸው ደግሞ ሌላኛው የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ ወጣት ውብሸት አስማማው ነው።
የከተማዋ እድገትና ውበት ከፍ ለማድረግ ከተማ እስተዳደሩ ለሚያደርገው ህገወጥን የመከላከል ተግባር አጋር በመሆን የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጿል።