ቀጥታ፡

የዳራሮ ባህላዊ እሴቶች አብሮነትና የልማት ተሳትፎን ያጠናክራሉ- የዲላ ነዋሪዎች

ዲላ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፦ የዳራሮ ባህላዊ እሴቶች የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር በማሳደግ የልማት ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እያገዙ መሆናቸውን በየዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የጌዴኦ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆኑው ዳራሮ በዞኑ ዋና ከተማ ዲላ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች መከበር የጀመረ ሲሆን እስከ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስም በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ይከበራል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት የዳራሮ ባህላዊ እሴቶች አብሮነትና የልማት ተሳትፎን እያጠናከሩ ነው።

የዲላ ከተማ  ነዋሪዎች መካከል ወጣት አቤነዘር ፀጋዬ እና ወይዘሮ ፈቲያ ጀማል እንደገለጹት የዳራሮ በዓልን ባህላዊ ይዘቱን ጠብቀው በማክበር እሴቶቹ እንዲተዋወቁና እንዲጠበቁ  እየተደረገ ሲሆን በዓሉ አብሮነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ የልማት ተሳትፏቸው እንዲጎለበት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ አብሮነትና መደጋገፍን ስለሚያጠናክር ለሀገራዊ አንድነት መጎልበት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀው፤ የዘንድሮውን የበዓል ተሳታፊዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛትና ለዲላ ከተማ ኮሪደር ልማት ድጋፍ በማድረግ መሳተፋቸውን ገልጿል።

የበዓሉ እሴቶች የአካባቢ ጥበቃ፣ ይቅርታ፣ ሰላምና አንድነትን ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ለትውልድ እንዲተላለፉም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የጌዴኦ ባህላዊ የባሌ ስርዓት መሪ አባገዳ ቢፎሚ ዋቆ በበኩላቸው ዳራሮ ከዘመን መለወጫነቱ ባለፈ የማንነት መገለጫና ጠቃሚ ሀገር በቀል እሴቶች የሚጸባረቁበት በተለይም ተፈጥሮን የመንከባከብና የማልማት እሴቶቹ ህብረተሰቡን ለልማት ለማነሳሳት ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።



የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደርቤ ጂኖ በበኩላቸው የዳራሮ በዓል የህዝቦችን አብሮነት በሚያጠናክር አግባብ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግም በዞኑ የተለያዩ ከተሞች ከ20 በላይ የልማት ፕሮጀክትች ተመርቀው ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም