ቀጥታ፡

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሻራችንን የማኖር ድርሻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ፤ጥር 21/2017 (ኢዜአ):-ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን የማኖር ድርሻቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአርባምንጭ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

የጋሞ ዞን ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ በአርባምንጭና በሌሎችም የዞኑ አካባቢዎች የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር ዘንድሮ ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቋል።

ከአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ዘውዲቱ ዛሃ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የማጠናቀቅ ታሪካዊ አደራ አለብን ብለዋል።

ግድቡ ታሪካዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ለፍጻሜ እስኪበቃ ድረስ የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታወቀዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ አሁንም እንደመቀጥሉ ጠቁመዋል።

ሌላኛው ወጣት ዘሪሁን መላኩ በበኩሉ፥ አባቶቻችን ጀግንነታቸውን በአድዋ እንዳረጋገጡ ሁሉ የእኛ ትውልድም የህዳሴ ግድብን ከፍጻሜ በማድረስ ጀግንነታችንን እናሳያለን ብሏል።

ግድቡ የሃይል አቅርቦታችንን ስለሚያሳድግ ቦንድ በመግዛት አሻራውን ማሳረፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እርስ በርሳችን ያስተሳሰረን የአንድነታችን ተምሳሌት ነው ያሉት ደግሞ አቶ ትርፋቸው ትፌ ናቸው።

የግድቡ ሂደት ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደምንችል ያረጋገጠ ታሪካዊ ፕሮጀክት በመሆኑ የግንባታው ቀሪ ስራዎች ለስኬት እስኪበቁ ቦንድ በመግዛት ተሳትፎቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ይህም የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ እቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የጋሞ ዞን ህዳሴ ግድብ ሕዘባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ዋንጃ ዋናቃ በበኩላቸው፥ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደቀጠለ ነው።

በዞኑ ከታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር 2017ዓ.ም ድረስ ከ130 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ በንቅናቄ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

የግድቡን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ በሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ የህዝቡ ምላሽ የሚደንቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ በጋሞ ዞን ከ284 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም