ቀጥታ፡

አምባሳደሮቹ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መከሩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፡- በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢትዮጵያ አምባሳደር መኩሪያ ጌታቸው እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአንጎላ አምባሳደር ሚጉዌል ዳ ኮስታ የሁለቱን ሀገራት ትብብር በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ እና አንጎላ የሁለትዮሽ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

ሀገራቱ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ እድሎችን ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

አንጎላ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር እያደረገች ያለው የማሸማገል ጥረት በውይይቱ ላይ መነሳቱን በኪንሻሳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም