ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ገዢና አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባት ረገድ ብልጽግና ፓርቲ የተሳካ ውጤት አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ገዢና አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባት ረገድ ብልጽግና ፓርቲ የተሳካ ውጤት አምጥቷል
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፦ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ገዢና አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባት ረገድ ብልጽግና ፓርቲ የተሳካ ውጤት ማምጣቱን በፓርቲው የተለያዩ ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች ገለጹ።
ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ገዢና አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑንም ጠቅሰዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ከፍያለው ተፈራ፤ ፓርቲው ሕብረ ብሔራዊ ጠንካራ ሀገር የመገንባት ስራዎችን መስራቱን ተናግረዋል።
በዚህም አንድነትን ማጎልበት የሚችሉና ወንድማማችነትን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ብሎም አብሮነትን የሚያጸኑ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በፓርቲው የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት የነበሩ ከፋፋይ እና አግላይ ትርክቶችን በማስተካከል አሰባሳቢና አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
የዜጎችን አንድነት የሚያጠናክሩ የጋራ ትርክቶችን በመገንባት ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ስንቅ የሚሆኑና ሀገርንም የሚገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ገዢና አሰባሳቢ ትርክቶችን በመገንባት የተሳካ ውጤት ማምጣቱንም ነው ያብራሩት።

በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መሐመድ ሻሌ፤ ብልጽግና ፓርቲ አግላይ የነበረን ስርዓት በማስቀረት አካታችነትን በተግባር እውን ያደረገ ህብ-ብሄራዊ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ብዝሃነትን የሚያጠናክር አሰባሳቢ ትርክት በመፍጠር ረገድ ሀገርን የሚያጸኑ ስኬቶች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ብልጽግና ተግዳሮቶችን በማሸነፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል በመፍጠር ወንድማማችነት እና እህትማማችነት በተግባር እንዲረጋገጥም በመስራት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ጠንካራ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ እንዲሆን ፓርቲው የተቋም ግንባታ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ሲሉም አቶ ይርጋ ሲሳይ አክለዋል።
ተቋማትን ለማጠናከር ሰፊ አደረጃጀቶች መሰራታቸውን ጠቁመው ዲጂታላይዜሽንን እንዲተገብሩም ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው ጠንካራ ሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለተቋማት ግንባታ የተሰጠው ትኩረት ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን መስራት የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
የተቋማትን ስኬታማነት ለማረጋገጥ የአሰራር ስርዓቶችን የማዘመን ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ነው ሃላፊዎቹ የተናገሩት።